am_obs/content/32.md

6.2 KiB

32. ኢየሱስ ርኵስ መንፈስ የያዘውን ሰውና የታመመችውን ሴት ፈወሰ

OBS Image

አንድ ቀን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ሐይቁን አቋርጠው የጌርጌሴኖን ሰዎች ወደሚኖሩበት አካባቢ ሄዱ።

OBS Image

ወደ ሐይቁ ማዶ በደረሱ ጊዜ ርኵስ መንፈስ የያዘው ሰው ሮጦ ወደ ኢየሱስ መጣ።

OBS Image

ይህ ሰው ማንም ሊቈጣጠረው የማይችል እጅግ ብርቱ ነበረ። ሰዎች እጆቹንና እግሮቹን እንኳ በሰንሰለት አስረውት ነበር፣ ነገር ግን ሰንሰለቱን ይበጣጥስ ነበር።

OBS Image

ሰውዬው በአካባቢው ባሉ መቃብሮች መካከል ይኖር ነበር። ይህ ሰው ቀኑንና ሌሊቱን ሁሉ ይጮኽ ነበር። ልብስ አይለብስም ነበር፣ ሰውነቱንም በተደጋጋሚ በድንጋይ ይቧጭር ነበር።

OBS Image

ሰውዬው ወደ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ፣ በፊቱ በጉልበቱ ወድቆ ሰገደለት። ኢየሱስ ርኵስ መንፈሱን፣ “ከዚህ ሰው ውጣ!” አለው።

OBS Image

ርኵስ መንፈሱ ያለበት ሰው ከፍ ባለ ድምፅ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፣ ከእኔ ምን ትፈልጋለህ? እባክህን አታሠቃየኝ!" ብሎ ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ። ከዚያም ኢየሱስ ርኵስ መንፈሱን፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፣ “ብዙዎች ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው” አለና መለሰ። (“ሌጌዎን” በሮማ ጦር ሠራዊት ብዙ ሺህ ወታደሮችን የያዘ ክፍል ነበር።)

OBS Image

ርኵሳን መናፍስቱ፣ “እባክህን ከዚህ አካባቢ አታርቀን!” ብለው ለመኑት። በአቅራቢያው ባለ ኮረብታ ላይ የእሪያ መንጋ ተሰማርቶ ነበር። ስለዚህ ርኵሳን መናፍስቱ ኢየሱስን፣ “እባክህን በዚህ ፈንታ ወደ እሪያዎቹ ስደደን!” ብለው ለመኑት። ኢየሱስ፣ “ሂዱ!” አላቸው።

OBS Image

ርኵሳን መናፍስቱ ከሰውዬው ወጡና ወደ እሪያዎቹ ገቡ። እሪያዎቹ ከአፋፉ ቊልቊል ሮጡና በሐይቁ ሰጠሙ። በመንጋው 2,000 ያህል እሪያዎች ነበሩ።

OBS Image

እሪያዎቹን ይጠብቁ የነበሩት ሰዎች የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ ወደ ከተማ ሮጡና ኢየሱስ ያደረገውን ነገር ላገኙት ሰው ሁሉ ተናገሩ። የከተማው ሰዎች መጡና ርኵሳን መናፍስት የነበሩበትን ሰው ዐዩ። ልብሱን ለብሶ እንደ ጤናማ ሰው ሆኖ በጸጥታ ተቀምጦ ነበር።

OBS Image

ሰዎቹ በጣም ፈርተው ነበርና ኢየሱስን እንዲሄድ ጠየቁት። ስለዚህ ኢየሱስ ጀልባ ውስጥ ገባና ለመሄድ ተዘጋጀ። ርኵን መናፍስት የነበሩበት ሰው ከኢየሱስ ጋር ለመሄድ ልመና አቀረበ።

OBS Image

ነገር ግን ኢየሱስ፣ “አይደለም፣ ወደ ቤትህ ሄደህ እግዚአብሔር ስላደረገልህ ነገር ሁሉና እንዴት እንደ ማረህ ለወዳጆችህና ለቤተ ሰብህ እንድትነግር እፈልጋለሁ” አለው።

OBS Image

ስለዚህ ሰውዬው ሄደና ኢየሱስ ስላደረገለት ነገር ለሁሉም ሰው ተናገረ። ታሪኩን የሰማ ሰው ሁሉ በአድናቆትና በአግራሞት ተሞላ።

OBS Image

ኢየሱስ ወደ ሐይቁ ማዶ ተመለሰ። እዚያ በደረሰ ጊዜ ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰበሰቡና አጨናነቁት። በሕዝቡ መካከል ለዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረች ሴት ነበረች። እንዲፈውሱአት ገንዘብዋን ሁሉ ለሐኪሞች ከፍላ ነበር፣ ነገር ግን ባሰባት።

OBS Image

ኢየሱስ ብዙ በሽተኞችን እንደ ፈወሰ ሰምታ ነበርና፣ “የኢየሱስን ልብስ ብቻ ብዳስስ ያኔ እኔም እንደምፈወስ እርግጠኛ ነኝ!” ብላ ዐሰበች። ስለዚህ ከኢየሱስ ኋላ መጣችና ልብሱን ዳሰሰች። ልብሱን እንደ ዳሰሰች ወዲያውኑ ደምዋ ቆመ!

OBS Image

ወዲያውኑ፣ ኢየሱስ ኃይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐወቀ። ስለዚህ ወደ ኋላ ዞረና፣ “ማን ነው የዳሰሰኝ?” ብሎ ጠየቀ። ደቀ መዛሙርቱ፣ “በዙሪያህ የተሰበሰቡና የሚያጋፉህ ብዙ ሰዎች አሉ። ‘ስለ ምን ማን ዳሰሰኝ’ ብለህ ትጠይቃለህ?” ብለው መለሱለት።

OBS Image

ሴቲቱ እየተንቀጠቀጠችና በጣም እየፈራች በኢየሱስ ፊት ተደፋች። ከዚያም ያደረገችውን፣ እንዲሁም የተፈወሰች መሆንዋን ነገረችው። ኢየሱስ፣ “እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ” አላት።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 8፡28-34፤ 9፡20-22፤ ማርቆስ 5፡1-20፤ 5፡24-34፤ ሉቃስ 8፡26-39፤ 8፡42-48።