am_obs/content/49.md

8.4 KiB

49. ዐዲሱ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን

OBS Image

አንድ መልአክ ማርያም ለተባለች ድንግል የእግዚአብሔርን ልጅ እንደምትወልድ ነገራት። ስለዚህ እርስዋ ገና ድንግል እያለች ወንድ ልጅ ወለደችና ኢየሱስ ብላ ሰየመችው። ስለዚህ ኢየሱስ አምላክም ሰውም ነው።

OBS Image

ኢየሱስ አምላክ መሆኑን የሚያረጋግጡ ብዙ ተአምራትን አደረገ። በውሃ ላይ ተራመደ፣ ማዕበልን ጸጥ አደረገ፣ ብዙ በሽተኞችን ፈወሰ፣ አጋንንትን አወጣ፣ ሙታንን አስነሣ፣ እንዲሁም አምስት እንጀራና ሁለት ትንንሽ ዓሣ ከ5,000 ለበለጡ ሰዎች እንዲበቃ አደረገ።

OBS Image

ደግሞም ኢየሱስ ታላቅ መምህር ነው፣ የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነም በሥልጣን ተናገረ። ራሳችሁን እንደምትወዱ ሌሎችን ሰዎችንም ውደዱ ብሎ አስተማረ።

OBS Image

ደግሞም እርሱ ሀብታችሁን ጨምሮ ማንኛውንም ነገር እንደምትወዱ እግዚአብሔርን መውደድ አለባችሁ ብሎ አስተማረ።

OBS Image

ኢየሱስ የእግዚአብሔር መንግሥት በዓለም ካለ ከማንኛውም ነገር ይልቅ የከበረች ነች አለ። ለማንኛውም ሰው እጅግ በጣም አስፈላጊው ነገር የእግዚአብሔር መንግሥት ወገን መሆን ነው። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ከኃጢአታችሁ መዳን አለባችሁ።

OBS Image

ኢየሱስ አንዳንድ ሰዎች ተቀብለውት እንደሚድኑ፣ ሌሎች ግን እንደማይቀበሉት አስተማረ። አንዳንድ ሰዎች እንደ መልካም መሬት ናቸው አለ። የኢየሱስን የምሥራች ተቀብለው ይድናሉ። ሌሎች ሰዎች የእግዚአብሔር ቃል ዘር እንደማይገባበትና ምንም ፍሬ እንደማያፈራ በመንገድ ዳር እንዳለ አለትማ መሬት ናቸው። እነዚያ ሰዎች ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን መልእክት የማይቀበሉና ወደ መንግሥቱ የማይገቡ ናቸው።

OBS Image

ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን በጣም እንደሚወድ አስተማረ። ይቅር ሊላቸውና ልጆቹ ሊያደርጋቸው ይፈልጋል።

OBS Image

ደግሞም ኢየሱስ እግዚአብሔር ኃጢአትን እንደሚጠላ ነግሮናል። አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ፣ ኃጢአቱ ዝርያዎቻቸውን ሁሉ ጐዳ። ከዚህ የተነሣ በዓለም ያለ ሁሉም ሰው ኃጢአት ይሠራል ከእግዚአብሔርም ይለያያል። ስለዚህ ሁሉም ሰው የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።

OBS Image

ነገር ግን በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።

OBS Image

በኃጢአታችሁ ምክንያት በደለኞች ናችሁና መሞት ይገባችኋል። እግዚአብሔር በእናንተ ላይ መቈጣት ነበረበት፣ ነገር ግን ቊጣውን በእናንተ ላይ በማፍስስ ፈንታ በኢየሱስ ላይ አፈሰሰው። ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ፣ የእናንተን ቅጣት ተቀበለ።

OBS Image

ኢየሱስ ከቶ ኃጢአት አላደረገም፣ ነገር ግን የእናንተን ኃጢአትና በዓለም ያለውን የእያንዳንዱን ሰው ኃጢአት ለማስወገድ መቀጣትንና ፍጹም መሥዋዕት ሆኖ መሞትን መረጠ። ኢየሱስ ራሱን ስለ ሠዋ፣ እግዚአብሔር ማንኛውንም ኃጢአት፣ አስከፊ የሆነውን ኃጢአት እንኳ ይቅር ማለት ይችላል።

OBS Image

መልካም ሥራዎች ሊያድኑአችሁ አይችሉም። ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት እንዲኖራችሁ ልታደርጉ የምትችሉት ምንም ነገር የለም። ኢየሱስ ብቻ ኃጢአታችሁን ሊያጥብ ይችላል። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን፣ በእናንተ ፈንታ በመስቀል ላይ መሞቱን እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው ብቻ ማመን አለባችሁ።

OBS Image

እግዚአብሔር በኢየሱስ የሚያምነውንና ጌታው አድርጎ የሚቀበለውን ማንኛውንም ሰው ያድናል። ባለ ጠጎች ሆኑ ወይም ድሆች፣ ወንድ ወይም ሴት፣ ሽማግሌ ወይም ወጣት፣ ወይም የትም ብትኖሩ ምንም አይደለም። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የቅርብ ግንኙነት ሊኖረው ይችል ዘንድ ይወዳችኋል በኢየሱስ እንድታምኑም ይፈልጋል።

OBS Image

ኢየሱስ እንድታምኑና እንድትጠመቁ ይጋብዛችኋል። ኢየሱስ መሲሕ፣ ብቸኛው የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ታምናላችሁ? ኃጢአተኞች መሆናችሁንና እግዚአብሔር ቢቀጣችሁ የተገባ መሆኑን ታምናላችሁ? ኢየሱስ ኃጢአታችሁን ለማስወገድ በመስቀል ላይ መሞቱን ታምናላችሁ?

OBS Image

በኢየሱስና እርሱ ለእናንተ በሠራው ሥራ ብታምኑ፣ እናንተ ክርስቲያኖች ናችሁ! እግዚአብሔር ከሰይጣንና ከጨለማ መንግሥት አውጥቶአችሁ በእግዚአብሔር የብርሃን መንግሥት ውስጥ አድርጎአችኋል። እግዚአብሔር ነገሮችን የምታደርጉበትን አሮጌውንና ኃጢአተኛውን መንገዳችሁን አስወግዶ ዐዲስና ጻድቅ የሆነ የአደራረግ መንገድ ሰጥቶአችኋል።

OBS Image

እናንተ ክርስቲያኖች ናችሁ፣ ኢየሱስ በሠራው ሥራ ምክንያት እግዚአብሔር ኃጢአታችሁን ይቅር ብሎአችኋል። አሁን እግዚአብሔር በጠላቶች ፈንታ የቅርብ ወዳጆች አድርጎ ይቈጥራችኋል።

OBS Image

የእግዚአብሔር ወዳጆችና የጌታ ኢየሱስ አገልጋዮች ከሆናችሁ፣ ኢየሱስ ለሚያስተምራችሁ ነገር ትታዘዛላችሁ። ክርስቲያኖች ብትሆኑም እንኳ፣ አሁንም ኃጢአት ለመሥራት ትፈተናላችሁ። ነገር ግን እግዚአብሔር የታመነ ነውና ኃጢአታችሁን ብትናዘዙ ይቅር እላችኋለሁ ይላል። ኃጢአትን የምትቃወሙበትን ብርታት ይሰጣችኋል።

OBS Image

እግዚአብሔር እንድትጸልዩ፣ ቃሉን እንድታጠኑ፣ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር እንድታመልኩ፣ ያደረገላችሁንም ለሌሎች እንድትነግሩ ይጠይቃችኋል። እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከእርሱ ጋር የጠለቀ ግንኙነት እንዲኖራችሁ ይረዱአችኋል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሮሜ 3፡21-26፤ 5፡1-11፤ ዮሐንስ 3፡16፤ ማርቆስ 16፡16፤ ቈላስይስ 1፡13-14፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17-21፤ 1ኛ ዮሐንስ 1፡5-10።