am_obs/content/48.md

7.4 KiB

48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው

OBS Image

እግዚአብሔር ዓለምን በፈጠረ ጊዜ ሁሉም ነገር ፍጹም ነበረ። ኃጢአት አልነበረም። አዳምና ሔዋን እርስ በርሳቸው ይዋደዱ ነበር፣ እግዚአብሔርንም ይወዱት ነበር። በሽታ ወይም ሞት አልነበረም። እግዚአብሔር ዓለም እንድትሆን የፈለገው እንደዚህ ነበር።

OBS Image

ሰይጣን በገነት ሔዋንን ያስት ዘንድ በእባቡ በኩል ተናገረ። ከዚያ በኋላ እርስዋና አዳም በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠሩ። እነርሱ ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት በምድር ያለ ሰው ሁሉ ይታመማል ይሞታልም።

OBS Image

አዳምና ሔዋን ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት ከዚያም የበለጠ መጥፎ ነገር እንኳ ሆነ። እነርሱ የእግዚአብሔር ጠላቶች ሆኑ። ከዚህ የተነሣ ከዚያን ጊዜ አነሥቶ ሁሉም ሰው በኃጢአት ባሕርይ ተወልዶአል ደግሞም የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል የነበረው ግንኙነት በኃጢአት ተቋረጠ። ነገር ግን እግዚአብሔር ያንን ግንኙነት የመመለስ ዕቅድ ነበረው።

OBS Image

ከሔዋን ዝርያዎች አንዱ የሰይጣንን ራስ እንደሚቀጠቅጥ፣ ሰይጣንም ሰኰናውን እንዲያቈስል እግዚአብሔር ተስፋ ሰጠ። ይህም ሰይጣን መሲሑን ይገድላል፣ ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ ገና ያስነሣዋል ማለት ነው፣ ከዚያም መሲሑ የሰይጣንን ኃይል ለዘላለም ይቀጠቅጠዋል። ከብዙ ዓመታት በኋላ እግዚአብሔር መሲሑ ኢየሱስ መሆኑን ገለጠ።

OBS Image

እግዚአብሔር ምድርን ሁሉ በጥፋት ውሃ ባጠፋ ጊዜ፣ በእርሱ ያመኑትን ሰዎች ለማዳን መርከብ አቀረበ። በተመሳሳይ መንገድ ሰው ሁሉ በኃጢአቱ ምክንያት መጥፋት ይገባው ነበር፣ ነገር ግን እግዚአብሔር በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ ለማዳን ኢየሱስን ሰጠ።

OBS Image

ለብዙ መቶ ዓመታት ካህናት ለኃጢአታቸው የሚገባቸውን ቅጣት ለማሳየት ስለ ሕዝቡ ያለ ማቋረጥ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ። ነገር ግን እነዚያ መሥዋዕቶች ኃጢአታቸውን ሊያስወግዱ አልቻሉም። ኢየሱስ ታላቁ ሊቀ ካህናት ነው። ከሌሎች ካህናት በተለየ ሁኔታ ራሱን በዓለም ላይ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ኃጢአት ማስወገድ የሚችል ብቸኛ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። ኢየሱስ ማንኛውም ሰው የሠራውን የእያንዳንዱን ኃጢአት ቅጣት ስለ ወሰደ ፍጹም ሊቀ ካህናት ነው።

OBS Image

እግዚአብሔር ለአብርሃም፣ “የምድር ሕዝብ ወገኖች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” ብሎ ነገረው። ኢየሱስ ከአብርሃም ትውልድ ነው። በእርሱ በኩል የሕዝብ ወገኖች ሁሉ ተባርከዋል፣ ምክንያቱም በኢየሱስ የሚያምን እያንዳንዱ ሰው ከኃጢአት ድኖአል፣ እንዲሁም የአብርሃም መንፈሳዊ ትውልድ ይሆናል።

OBS Image

ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ እግዚአብሔር ለአብርሃም በነገረው ጊዜ፣ እግዚአብሔር በልጁ በይስሐቅ ፈንታ የመሥዋዕት በግ አቀረበ። ሁላችንም በኃጢአታችን መሞት ይገባናል! ነገር ግን እግዚአብሔር መሥዋዕት ሆኖ በእኛ ቦታ እንዲሞት የእግዚአብሔር በግ የሆነውን ኢየሱስን ሰጠ።

OBS Image

እግዚአብሔር በግብፅ ላይ የመጨረሻውን መቅሠፍት በላከ ጊዜ እንከን የሌለበት ጥቦት እንዲያርዱና ደሙን በበሩ መቃንና ጉበን ላይ እንዲረጩት ለእስራኤላውያን ቤተ ሰቦች ተናገረ። እግዚአብሔር ደሙን ባየ ጊዜ ቤቶቹን አልፎ ሄደ በኵር ልጆቻቸውንም አልገደለም። ይህ ታሪካዊ ድርጊት ፋሲካ ተብሎአል።

OBS Image

ኢየሱስ የፋሲካ በጋችን ነው። እርሱ ፍጹምና ያለ ኃጢአት ነው በፋሲካ በዓል ጊዜም ተገደለ። ማንኛውም ሰው በኢየሱስ በሚያምንበት ጊዜ፣ የኢየሱስ ደም ለዚያ ሰው ኃጢአት ክፍያ ነው፣ የእግዚአብሔር ቅጣትም በዚያ ሰው ላይ ያልፋል።

OBS Image

እግዚአብሔር የተመረጡ ሕዝቡ ከነበሩት ከእስራኤላውያን ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ነገር ግን አሁን እግዚአብሔር ለሁሉም ሰው የሚሆን ዐዲስ ቃል ኪዳን አድርጎአል። በዚህ ዐዲስ ቃል ኪዳን ምክንያት ከማንም ሕዝብ ወገን የሆነ ማንኛውም ሰው በኢየሱስ በማመን የእግዚአብሔር ሕዝብ ወገን መሆን ይችላል።

OBS Image

ሙሴ የእግዚአብሔርን ቃል ያወጀ ታላቅ ነቢይ ነበረ። ኢየሱስ ግን ከሁሉም የላቀ ነቢይ ነው። እርሱ አምላክ ነው፣ ስለዚህ እርሱ ያደረገውና የተናገረው ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር ሥራና ቃል ነው። ስለዚህ ነው ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል ተብሎ የሚጠራው።

OBS Image

ከዝርያዎቹ አንዱ ንጉሥ ሆኖ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ለዘላለም እንደሚገዛ እግዚአብሔር ለንጉሥ ዳዊት ተስፋ ሰጠው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅና መሲሑ ስለሆነ፣ ለዘላለም መግዛት የሚችል ያ ልዩ የዳዊት ዘር ነው።

OBS Image

ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ ነበር፣ ኢየሱስ ግን የፍጥረት ዓለም ሁሉ ንጉሥ ነው! ተመልሶ ይመጣና በፍትሕና በሰላም መንግሥቱን ለዘላለም ይገዛል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘፍጥረት 1-3፤ 6፤ 14፤ 22፤ ዘጸአት 12፣ 20፤ 2ኛ ሳሙኤል 7፤ ዕብራውያን 3፡1-6፤ 4፡14-5፡10፤ 7፡1-8፡13፤ 9፡11-10፡18፤ ራእይ 21።