am_obs/content/47.md

6.5 KiB

47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ

OBS Image

ሳውል በሮማ የንጉሠ ነገሥት ግዛት ሁሉ በሚጓዝበት ጊዜ፣ ሮማዊ ስሙን “ጳውሎስ”ን መጠቀም ጀመረ። አንድ ቀን ጳውሎስና ጓደኛው ሲላስ ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን የምሥራች ሊያውጁ ወደ ፊልጵስዩስ ከተማ ሄዱ። ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ተሰበሰቡበት ከከተማይቱ ውጭ በወንዙ አጠገብ ወዳለ ስፍራ ሄዱ። በዚያ ነጋዴ የነበረች ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት አገኙ። እርስዋ እግዚአብሔርን ትወድና ታመልክ ነበር።

OBS Image

ስለ ኢየሱስ የሚነገረውን መልእክት እንድታምን እግዚአብሔር የልድያን ልብ ከፈተላት፤ እርስዋና ቤተ ሰብዋ ተጠመቁ፣ በቤትዋ እንዲኖሩ ጳውሎስንና ሲላስን ጋበዘቻቸው፣ ስለዚህ እነርሱ ከእርስዋና ከቤተ ሰብዋ ጋር ኖሩ።

OBS Image

ጳውሎስና ሲላስ ብዙ ጊዜ በጸሎት ስፍራ ከሰዎች ጋር ይገናኙ ነበር። በየዕለቱ ወደዚያ ሲሄዱ ጋኔን የያዛት አንዲት ባሪያ ልጃገረድ ትከተላቸው ነበር። እርሷም በዚህ ጋኔን አማካይነት ስለ መጪው ጊዜ ለሰዎች ትተነብይላቸው ነበር፣ ስለዚህ በጥንቈላ ለጌቶችዋ ብዙ ገንዘብ ታስገኝ ነበር።

OBS Image

ባሪያዪቱ ልጃገረድ እነርሱ ሲዘዋወሩ እየተከተለቻቸው፣ “እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው። የመዳንን መንገድ ይነግሩአችኋል!” በማለት መጮህዋን ቀጠለች። ጳውሎስ እስኪቈጣ ድረስ ይህንን ደጋግማ አደረገች።

OBS Image

በመጨረሻም አንድ ቀን ባሪያዪቱ ልጃገረድ መጮኽ በጀመረች ጊዜ ጳውሎስ ወደ እርስዋ ዘወር አለና በእርስዋ የነበረውን ጋኔን፣ “በኢየሱስ ስም፣ ከእርስዋ ውጣ” አለው። ወዲያውኑ ጋኔኑ ለቀቃት።

OBS Image

የባሪያዪቱ ልጃገረድ ጌቶች የነበሩት ሰዎች በጣም ተቈጡ! ያለ ጋኔኑ ባሪያዪቱ ልጅ ስለ ሰዎች መጪ ጊዜ መናገር እንደማትችል ዐወቁ። ይህም ሰዎች የሚደርስባቸውን ነገር ትነግራቸው ዘንድ ስለማትችል ለጌቶችዋ ገንዘብ አይከፍሉም ማለት ነው።

OBS Image

ስለዚህ የባሪያዪቱ ልጃገረድ ጌቶች ጳውሎስንና ሲላስን ወደ ሮማ ባለ ሥልጣናት ወሰዱአቸው፣ እነርሱም ደብድበው ወደ እስር ቤት ጣሉአቸው።

OBS Image

እነርሱም ጳውሎስንና ሲላስን በእስር ቤት ውስጠኛ ክፍል አሰሩአቸው እግሮቻቸውን እንኳ ከግንድ ጋር አሰሩአቸው። ሆኖም ግን እከለ ሌሊት ላይ ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር ዘመሩ።

OBS Image

በድንገት ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ሆነ! የእስር ቤቱ በሮች ሁሉ ወለል ብለው ተከፈቱ፣ የእስረኞቹ ሁሉ ሰንሰለቶችም ረገፉ።

OBS Image

የእስር ቤቱ ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቃ፣ የእስር ቤቱ በሮች ሁሉ መከፈታቸውን ባየ ጊዜ ፈራ! እስረኞቹ ሁሉ ያመለጡ መሰለው፣ ስለዚህ ራሱን ለመግደል ዐሰበ። (እስረኞቹ እንዲያመልጡ ካደረገ የሮማ ባለ ሥልጣናት እንደሚገድሉት ዐወቀ።) ነገር ግን ጳውሎስ ዐየውና፣ “ተው! ራስህን አትጕዳ። ሁላችንም እዚህ አለን” ብሎ ጮኸበት።

OBS Image

የእስር ቤቱ ጠባቂ ወደ ጳውሎስና ሲላስ እየመጣ እያለ ተንቀጠቀጠና፣ “እድን ዘንድ ምን ላድርግ?” ብሎ ጠየቀ። ጳውሎስ፣ “በጌታ በኢየሱስ እመን፣ አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ” ብሎ መለሰለት። ከዚያም የእስር ቤት ጠባቂው ጳውሎስንና ሲላስን ወደ ቤቱ ወሰዳቸውና ቊስላቸውን አጠበላቸው። ጳውሎስ በቤቱ ለነበሩት ሁሉ ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን የምሥራች ሰበከላቸው።

OBS Image

የእስር ቤት ጠባቂውና መላው ቤተ ሰቡ በኢየሱስ አምነው ተጠመቁ። ከዚያም የእስር ቤት ጠባቂው ለጳውሎስና ለሲላስ ምግብ አቀረበላቸውና በአንድነት ደስ አላቸው፡

OBS Image

በማግስቱ የፊልጵስዩስ መሪዎች ጳውሎስና ሲላስን ከእስር ቤት ፈቱአቸውና ከፊልጵስዩስ እንዲሄዱ ጠየቁአቸው። ጳውሎስና ሲላስ ልድያንና አንዳንድ ሌሎች ወዳጆችን ጐበኙና ከተማይቱን ለቀው ሄዱ። ስለ ኢየሱስ የሚናገረው የምሥራች መስፋፋቱን ቀጠለ ቤተ ክርስቲያንም ማደግዋን ቀጠለች።

OBS Image

ጳውሎስና ሌሎች ክርስቲያን መሪዎች ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን የምሥራች እየሰበኩና እያስተማሩ ወደ ብዙ ከተሞች ተጓዙ። ደግሞም በአብያተ ክርስቲያናቱ ላሉ አማኞች ሊያበረታቱአቸውና ሊያስተምሩአቸው ብዙ መልእክቶችን ጻፉላቸው። ከእነዚህ መልእክቶች አንዳንዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ያሉት መጻሕፍት ሆኑ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሐዋርያት ሥራ 16፡11-40።