am_obs/content/46.md

5.8 KiB

46. ጳውሎስ ክርስቲያን ሆነ

OBS Image

ሳውል እስጢፋኖስን የገደሉት ሰዎች ልብስ ይጠብቅ የነበረ ወጣት ነበረ። በኢየሱስ አላመነም፣ ስለዚህም አማኞችን አሳደደ። ወንዶችንና ሴቶችን እየያዘ ወደ እስር ቤት ለመጨመር በኢየሩሳሌም ከቤት ወደ ቤት ሄደ። ሊቀ ካህናቱ በዚያ ያሉትን ክርስቲያኖች ይይዝና ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ ያመጣቸው ዘንድ ወደ ደማስቆ ከተማ እንዲሄድ ለሳውል ፈቃድ ሰጠው።

OBS Image

ሳውል ወደ ደማስቆ በመጓዝ ላይ እያለ፣ ከሰማይ ብሩህ ብርሃን በዙሪያው ሁሉ አበራ፣ እርሱም ወደ መሬት ወደቀ። አንድ ሰው፣ “ሳውል! ሳውል! ስለምን ታሳድደኛለህ?” ሲለው ሰማ። ሳውል፣ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ማን ነህ?” ብሎ ጠየቀ። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰለት፣ “እኔ ኢየሱስ ነኝ። አንተ እያሳደድከኝ ነው!” ብሎ መለሰለት።

OBS Image

ሳውል በተነሣ ጊዜ፣ ማየት ተሳነው። ወዳጆቹ ወደ ደማስቆ እየመሩ ወሰዱት። ሳውል ለሦስት ቀናት ምንም አልበላም ወይም አልጠጣም።

OBS Image

በደማስቆ ሐናንያ የተባለ ደቀ መዝሙር ነበረ። እግዚአብሔር ለሐናንያ፣ “ሳውል ወዳለበት ቤት ሂድ። እንደ ገና ያይ ዘንድ እጅህን ጫንበት” አለው። ሐናንያ ግን፣ “ጌታ ሆይ፣ ይህ ሰው አማኞችን እንዴት እንዳሳደደ ሰምቼአለሁ” አለ። እግዚአብሔር፣ “ሂድ! ለአይሁዶችና ከሌሎች ሕዝቦች ለሆኑ ወገኖች ስሜን እንዲያውጅ መርጬዋለሁ። ስለ ስሜ ብዙ መከራ ይቀበላል” አለው።

OBS Image

ስለዚህ ሐናንያ ወደ ሳውል ሄደ። እጆቹን ጫነበት፣ እንዲህም አለ፣ “ወደዚህ ስትመጣ የታየህ ኢየሱስ፣ እንደ ገና ታይና በመንፈስ ቅዱስ ትሞላ ዘንድ ወዳንተ ላከኝ።” ሳውል ወዲያውኑ ማየት ቻለ፣ ሐናንያም አጠመቀው። ከዚያ በኋላ ሳውል ምግብ በላ፣ በረታም።

OBS Image

ሳውል ወዲያውኑ፣ “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው!” በማለት በደማስቆ ለነበሩ አይሁድ መስበክ ጀመረ። አይሁዶች አማኞችን ለማጥፋት የሞከረው ሰው አሁን ደግሞ በኢየሱስ በማመኑ ተደነቁ! ሳውል ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን በማረጋገጥ አይሁዶችን አሳመነ።

OBS Image

ከብዙ ቀናት በኋላ አይሁዶች ሳውልን ለመግደል ዐቀዱ። ይገድሉት ዘንድ በከተማይቱ በሮች የሚጠባበቁትን ሰዎች ላኩ። ነገር ግን ሳውል ስለ ዕቅዱ ሰማ፣ ወዳጆቹም እንዲያመልጥ ረዱት። አንድ ሌሊት በቅርጫት አድርገው በከተማዪቱ ቅጥር አወረዱት። ሳውል ከደማስቆ ካመለጠ በኋላ ስለ ኢየሱሰ መስበኩን ቀጠለ።

OBS Image

ሳውል ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመገናኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፣ እነርሱ ግን ፈሩት። በዚያን ጊዜ በርናባስ የተባለ አማኝ ሳውልን ወደ ሐዋርያቱ ወሰደውና ሳውል በደማስቆ እንዴት በድፍረት እንደ ሰበከ ነገራቸው። ከዚያ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ሳውልን ተቀበሉት።

OBS Image

በኢየሩሳሌም ከነበረው ስደት የሸሹ አንዳንድ አማኞች ወደ አንጾኪያ ርቀው ሄዱና ስለ ኢየሱስ ሰበኩ። በአንጾኪያ የነበሩት ብዙዎቹ ሰዎች አይሁዶች አልነበሩም፣ ነገር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ፣ በጣም ብዙዎቻቸው ደግሞ አማኞች ሆኑ። በርናባስና ሳውል እነዚህን ዐዳዲስ አማኞች በተጨማሪ ስለ ኢየሱስ ሊያስተምሯቸውና ቤተ ክርስቲያንን ሊያጠናክሩ ወደዚያ ሄዱ። በኢየሱስ የሚያምኑ መጀመሪያ ጊዜ በአንጾኪያ “ክርስቲያኖች” ተባሉ።

OBS Image

አንድ ቀን በአንጾኪያ የነበሩ ክርስቲያኖች እየጾሙና እየጸለዩ እያሉ መንፈስ ቅዱስ፣ “የጠራኋቸውን ሥራ እንዲሠሩ በርናባስንና ሳውልን ለዩልኝ” አላቸው። ስለዚህ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ለበርናባስና ለሳውል ጸለዩላቸው፣ እጆቻቸውንም ጫኑባቸው። ከዚያም በሌሎች ብዙ ቦታዎች ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን የምሥራች እንዲሰብኩ ላኩአቸው። በርባናስና ሳውል ከተለያዩ የሕዝብ ወገኖች የሆኑ ሰዎችን አስተማሩ፣ ብዙ ሰዎችም በኢየሱስ አመኑ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሐዋርያት ሥራ 8፡3፤ 9፡1-31፤ 11፡19-26፤ 13፡1-3።