am_obs/content/45.md

6.6 KiB

45. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን

OBS Image

በጥንትዋ ቤተ ክርስቲያን ከነበሩት መሪዎች አንዱ እስጢፋኖስ ተብሎ የሚጠራ ሰው ነበር። እርሱ መልካም ስም ያለውና መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላበት ሰው ነበር። እስጢፋኖስ ብዙ ተአምራትን ያደረገና ሰዎች በኢየሱስ እንዲያምኑ አሳማኝ ምክንያት የሚያቀርብ ሰው ነበር።

OBS Image

አንድ ቀን እስጢፋኖስ ስለ ኢየሱስ በሚያስተምርበት ጊዜ፣ በኢየሱስ ያላመኑ አንዳንድ አይሁድ ከእስጢፋኖስ ጋር መከራከር ጀመሩ። በጣም ተቈጡና ስለ እስጢፋኖስ ለሃይማኖት መሪዎች ዋሽተው ተናገሩ። “ስለ ሙሴና ስለ እግዚአብሔር ክፉ ነገሮችን ሲናገር ሰምተነዋል!” አሉ። ስለዚህ የሃይማኖት መሪዎቹ እስጢፋኖስን ያዙትና ተጨማሪ የሐሰት ምስክሮች ስለ እስጢፋኖስ ዋሽተው ወደተናገሩበት ወደ ሊቀ ካህናቱና ወደ ሌሎቹ የአይሁድ መሪዎች አመጡት።

OBS Image

ሊቀ ካህናቱ እስጢፋኖስን፣ “እነዚህ ነገሮች እውነት ናቸውን?” ብሎ ጠየቀው። እስጢፋኖስ ከአብርሃም ዘመን ጀምሮ እስከ ኢየሱስ ዘመን ድረስ እግዚአብሔር ስላደረጋቸው ብዙ ታላላቅ ነገሮች፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር ሕዝብ በተከታታይ በእርሱ ላይ ስለ ማመፃቸው በማስታወስ መልስ ሰጠ። ከዚያም እንዲህ አለ፣ “እናንተ አንገተ ደንዳኖችና ዓመፀኞች ሕዝብ ልክ ቅድማያቶቻችሁ እግዚአብሔርን እንደ ተቃወሙትና ነቢያቱን እንደ ገደሉ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ። እናንተ ግን ከእነርሱ ይልቅ የባሰ ነገር አድርጋችኋል። መሲሑን ገድላችኋል!”

OBS Image

የሃይማኖት መሪዎቹ ይህንን በሰሙ ጊዜ፣ ጆሮአቸውን እስኪደፍኑና ከፍ ባለ ድምፅ እስኪጮኹ ድረስ በጣም ተቈጡ። እስጢፋኖስን ከከተማይቱ ውጪ ጐተቱትና ሊገድሉት በድንጋይ ወገሩት።

OBS Image

እስጢፋኖስ በመሞት ላይ እያለ፣ “ኢየሱስ ሆይ፣ ነፍሴን ተቀበላት” ብሎ ጮኸ። ከዚያም በጉልበቱ ተንበረከከና፣ “ጌታ ሆይ፣ ይህንን ኃጢአት አትቊጠርባቸው” ብሎ እንደ ገና ጮኸ። ከዚያ በኋላ ሞተ።

OBS Image

ሳውል የተባለ ወጣት እስጢፋኖስን ከገደሉት ሰዎች ጋር ተስማማና በእርሱ ላይ ድንጋይ በሚወረውሩበት ጊዜ ልብሳቸውን ይጠብቅ ነበር። በዚያን ዕለት በኢየሩሳሌም የነበሩ ብዙ ሰዎች የኢየሱስን ተከታዮች ማሳደድ ጀመሩ፣ ስለዚህ አማኞቹ ወደ ሌሎች ስፍራዎች ሸሹ። ነገር ግን ስደቱ ቢኖርም እንኳ፣ በሄዱበት ስፍራ ሁሉ ስለ ኢየሱስ ሰበኩ።

OBS Image

ፊልጶስ የተባለ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር በስደቱ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ከሸሹት አማኞች አንዱ ነበር። ወደ ሰማርያ ሄዶ ስለ ኢየሱስ ሰበከና ብዙ ሰዎች ዳኑ። ከዚያ በኋላ አንድ ቀን ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ በምድረ በዳ ወዳለ አንድ መንገድ እንዲሄድ ለፊልጶስ ነገረው። ፊልጶስ በመንገዱ በመሄድ ላይ እያለ አንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ባለ ሥልጣን በሰረገላው ሲሄድ ዐየ። ወደዚህ ሰው ሄዶ እንዲያነጋግረው መንፈስ ቅዱስ ለፊልጶስ ነገረው።

OBS Image

ፊልጶስ ወደ ሰረገለው በቀረበ ጊዜ፣ ኢትዮጵያዊው ነቢዩ ኢሳይያስ ከጻፈው ውስጥ አንዱን ክፍል ሲያነብ ሰማ። ሰውዬው እንዲህ አነበበ፣ “እንደሚታረድ በግ ነዱት፣ በግ ዝም እንደሚል አንድም ቃል አልተናገረም። በፍርድ ተወሰደ፣ አላከበሩትምም። ከሕያዋን ምድር አስወገዱት።”

OBS Image

ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን፣ “የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” ብሎ ጠየቀው። ኢትዮጵያዊው፣ “አይደለም። የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር ላስተውለው አልችልም። እባክህን ናና ከጐኔ ተቀመጥ። ኢሳይያስ የጻፈው ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ ሰው?”

OBS Image

ኢሳይያስ የጻፈው ስለ ኢየሱስ መሆኑን ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው አብራራለት። ደግሞም ፊልጶስ ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን የምሥራች ሊነግረው ሌሎች የእግዚአብሔር ቃል ክፍሎችን ተጠቀመ።

OBS Image

ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው እንደ ተጓዙ፣ ውሃ ወዳለበት ስፍራ ደረሱ። ኢትዮጵያዊው፣ “እነሆ፣ በዚያ ቦታ ውሃ አለ! ልጠመቅን? አለ። ለነጂውም ሰረገላውን እንዲያቆመው ነገረው።

OBS Image

ስለዚህ ወደ ውሃው ወረዱ፣ ፊልጶስም ኢትዮጵያዊውን አጠመቀው። ከውሃው ከወጡ በኋላ መንፈስ ቅደስ በድንገት ፊልጶስን ወደ ሌላ ስፍራ ነጠቀው፤ ስለ ኢየሱስ ለሰዎች መናገሩንም ቀጠለ።

OBS Image

ኢትዮጵያዊው ኢየሱስን በማወቁ እየተደሰተ ወደ አገሩ ለመመለስ ጕዞውን ቀጠለ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሐዋርያት ሥራ 6፡8-8፡5፤ 8፡26-40።