am_obs/content/43.md

5.3 KiB
Raw Permalink Blame History

43. ቤተ ክርስቲያን ተጀመረች

OBS Image

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ እንዳዘዛቸው በኢየሩሳሌም ቆዩ። በዚያ የነበሩት አማኞች ለመጸለይ ያለ ማቋረጥ ተሰበሰቡ።

OBS Image

አይሁድ በያመቱ ከፋሲካ በኋላ ባሉት 50 ቀናት ጴንጤቆስጤ ተብሎ የሚጠራ አስፈላጊ ቀን ያከብሩ ነበር። ጴንጤቆስጤ አይሁድ የመከር በዓልን የሚያከብሩበት ቀን ነበር። አይሁድ ጴንጤቆስጤን በአንድነት ለማክበር ከመላው ዓለም ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበር። በዚህ ዓመት፣ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ የጴንጤቆስጤ ጊዜ መጣ።

OBS Image

አማኞቹ ሁሉ በአንድነት ተሰብስበው እያሉ፣ በድንገት የነበሩበት ቤት ድምፅ በመሰለ ብርቱ ነፋስ ተሞላ። ከዚያም በአማኞቹ ሁሉ ራስ ላይ የእሳት ነበልባል የሚመስል ነገር ታየ። ሁላቸውም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉና በሌሎች ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ።

OBS Image

በኢየሩሳሌም የነበሩት ሰዎች ድምፅን በሰሙ ጊዜ፣ በመሆን ላይ የነበረውን ነገር ለማየት በብዛት መጡ። አማኞቹ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራዎች ሲያውጁ ሰዎቹ በሰሙ ጊዜ እነዚህን ነገሮች በገዛ ራሳቸው ቋንቋ በመስማታቸው ተደነቁ።

OBS Image

አንዳንዶቹ ሰዎች ደቀ መዛሙርቱ ሰክረዋል ብለው ወቀሱአቸው። ነገር ግን ጴጥሮስ ቆመና እንዲህ አላቸው፣ “ስሙኝ! እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም! እግዚአብሔር በነቢዩ ኢዮኤል ‘በመጨረሻው ቀን መንፈሴን አፈስሳለሁ! ያለው ትንቢት በዚህ ይፈጸማል።

OBS Image

“የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ እናንተ እንዳያችሁትና አስቀድማችሁ እንደምታውቁት ኢየሱስ በእግዚአብሔር ኃይል ብዙ ታላላቅ ምልክቶችንና ድንቆችን ያደረገ ሰው ነው። ነገር ግን እናንተ ሰቀላችሁት!”

OBS Image

“ኢየሱስ ቢሞትም እንኳ እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው። ይህም ‘ቅዱስህንም በመቃብር መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም’ የሚለው ትንቢት ፍጻሜ ነው። እግዚአብሔር ኢየሱስን ሕያው አድርጎ እንዳስነሣው እኛ ምስክሮች ነን።”

OBS Image

“ኢየሱስ አሁን በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ከፍ ብሎአል። ደግሞም ኢየሱስ ልክ ተስፋ እንደ ሰጠው መንፈስ ቅዱስን ልኮአል። አሁን የምታዩአቸውንና የምትሰሙአቸውን ነገሮች መንፈስ ቅዱስ ነው ያደረጋቸው።

OBS Image

“ይህንን ኢየሱስን ሰቀላችሁት። ነገር ግን እግዚአብሔር ኢየሱስን ጌታና መሲሕ እንዳደረገው በእርግጥ እወቁ!”

OBS Image

ጴጥሮስን ይሰሙ የነበሩት ሰዎች በተናገራቸው ነገሮች በእጅጉ ተነኩ። ስለዚህ ጴጥሮስንና ደቀ መዛሙርቱን፣ “ወንድሞች ሆይ፣ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁአቸው።

OBS Image

ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፣ “እግዚአብሔር ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ እያንዳንዳችሁ ንስሐ ግቡና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ። ከዚያ በኋላ እርሱ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ደግሞ ይሰጣችኋል።”

OBS Image

3000 የሚያህሉ ሰዎች ጴጥሮስ የተናገረውን አምነው የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሆኑ። እነርሱ ተጠምቀው በኢየሩሳሌም ያለችው ቤተ ክርስቲያን አባል ሆኑ።

OBS Image

ደቀ መዛሙርቱ ያለ ማቋረጥ የሐዋርያትን ትምህርት ሰሙ፣ አብረው ጊዜ አሳለፉ፣ አብረው በሉ፣ አንዳቸው ለሌላኛው ጸለዩ። አብረው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፣ የነበራቸውንም ነገር ሁሉ እርስ በርስ ተካፈሉ። ሁሉም ሰው ስለ እነርሱ መልካም ያስብ ነበር። በየዕለቱ ብዙ ሰዎች አማኞች ሆኑ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሐዋርያት ሥራ 2።