am_obs/content/42.md

6.1 KiB

42. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ተመለሰ

OBS Image

ኢየሱስ ከሙታን በተነሣበት ቀን ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱ በአቅራቢያው ወዳለች ከተማ እየሄዱ ነበር። ሲጓዙም፣ በኢየሱስ ላይ ስለ ደረሰው ነገር ተነጋገሩ። እርሱ መሲሕ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገው ነበር፣ ነገር ግን ያኔ እርሱ ተገደለ። አሁን ሴቶቹ እንደ ገና ሕያው ሆኖአል አሉ። ሁለቱ ደቀ መዛሙርት የሚያምኑትን ነገር ዐላወቁም።

OBS Image

ኢየሱስ ወደ እነርሱ ቀረበና አብሮአቸው ይጓዝ ጀመር፣ እነርሱ ግን ዐላወቁትም። ስለ ምን ይነጋገሩ እንደ ነበረ ጠየቃቸው፣ እነርሱም ባለፉት ጥቂት ቀናት ኢየሱስን በሚመለከት ስለ ሆኑት አስደናቂ ነገሮች ሁሉ ነገሩት። በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር ከማያውቅ እንግዳ ጋር ይነጋገሩ እንደ ነበር ዐሰቡ።

OBS Image

ከዚያም ኢየሱስ፣ ስለ መሲሑ የእግዚአብሔር ቃል የተናገረውን አብራራላቸው። መሲሑ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚገደል፣ ነገር ግን በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ ነቢያት የተናገሩትን አስታወሳቸው። ሁለቱ ሰዎች ሊያድሩባት ወዳሰቡአት ከተማ ሲደርሱ፣ ጊዜው ሊመሽ ምንም ያህል አልቀረውም ነበር።

OBS Image

ሁለቱ ሰዎች ከእነርሱ ጋር እንዲያድር ጋበዙት፣ እርሱም ግብዣቸውን ተቀበለ። እራት ለመብላት በተዘጋጁ ጊዜ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ እግዚአብሔርን አመሰገነ፣ ከዚያም ቈረሰው። በድንገትም ኢየሱስ መሆኑን ዐወቁ። ነገር ግን በዚያን ጊዜ እርሱ ከዓይናቸው ተሰወረ።

OBS Image

ሁለቱ ሰዎች፣ “ኢየሱስ ነው! የእግዚአብሔርን ቃል ሲያብራራልን ልባችን ሲቃጠልብን የነበረው ስለዚህ ነው!” ተባባሉ። ወዲያውኑ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። በደረሱ ጊዜም ለደቀ መዛሙርቱ፣ “ኢየሱስ ሕያው ነው! ዐይተነዋል!” ብለው ነገሩአቸው።

OBS Image

ደቀ መዛሙርቱ እየተነጋገሩ እያሉ፣ ኢየሱስ በድንገት በነበሩበት ክፍል በመካከላቸው ታየና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ መሰላቸው፣ ኢየሱስ ግን፣ “ለምን ትፈራላችሁ ትጠራጠራላችሁም? እጆቼንና እግሮቼን እዩ። መናፍስት እንደ እኔ አካል የላቸውም” አላቸው። መንፈስ አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚበላ ነገር እንዲሰጡት ጠየቃቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቊራጭ ሰጡት፣ በላም።

OBS Image

ኢየሱስም፣ “በእግዚአብሔር ቃል ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም አለበት ብዬ ነግሬአችኋለሁ” አለ። በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲረዱ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው። “መሲሑ መከራ እንደሚቀበል፣ እንደሚሞት፣ በሦስተኛው ቀን ከሙታን እንደሚነሣ ከረጅም ዘመን በፊት ተጽፎአል” አላቸው።

OBS Image

“ደግሞም በመጻሕፍት የኃጢአታቸውን ይቅርታ ለማግኘት ሰዎች ሁሉ ንስሐ ይገቡ ዘንድ ደቀ መዛሙርቴ እንደሚያውጁ ተጽፎአል። እነርሱ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ይህን ያደርጋሉ፣ ከዚያም በሁሉም ስፍራ ወዳሉ የሕዝብ ወገኖች ሁሉ ይሄዳሉ። እናንተ የእነዚህ ነገሮች ምስክሮች ናችሁ።

OBS Image

በቀጣዮቹ አርባ ቀናት ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ታያቸው። አንዴ ከ500 ለሚበልጡ ሰዎች በአንድ ጊዜ ታይቶአል! ሕያው መሆኑን በብዙ መንገድ ለደቀ መዛሙርቱ አረጋገጠላቸው፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም አስተማራቸው።

OBS Image

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፣ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል። ስለዚህ ሂዱ፣ የሕዝብ ወገኖችን ሁሉ በአብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲፈጽሙ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው። እኔ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር እንደምሆን አስታውሱ።”

OBS Image

ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ ከአርባ ቀናት በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፣ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በመጣ ጊዜ አባቴ ኃይልን እስኪሰጣችሁ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ” አላቸው። ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ወጣ፣ ደመናም ከዓይናቸው ሰወረችው። ኢየሱስ በፍጥረት ሁሉ ላይ ሊገዛ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 28፡16-20፤ ማርቆስ 16፡12-20፤ ሉቃስ 24፡13-53፤ ዮሐንስ 20፡19-23፤ የሐዋርያት ሥራ 1፡1-11።