am_obs/content/41.md

3.5 KiB

41. እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሙታን አስነሣው

OBS Image

ወታደሮቹ ኢየሱስን ከሰቀሉት በኋላ፣ የማያምኑት የአይሁድ መሪዎች ጲላጦስን፣ “ያ ውሸታም፣ ኢየሱስ፣ ከሦስት ቀን በኋላ ከሙታን እነሣለሁ ብሎአል። ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን እንዳይሰርቁትና ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ ለማረጋገጥ አንድ ሰው መቃብሩን መጠበቅ አለበት” አሉት።

OBS Image

ጲላጦስ፣ “አንዳንድ ወታደሮችን ውሰዱና መቃብሩን በተቻለ መጠን እንዲጠበቅ አድርጉ” አለ። ስለዚህ በመቃብሩ መግቢያ ባለው ድንጋይ ላይ ማኅተም አደረጉና ሥጋውን ማንም እንዳይሰርቀው ለማረጋገጥ በዚያ ወታደሮችን አቆሙ።

OBS Image

ኢየሱስ ከተሰቀለ በኋላ የነበረ ቀን ሰንበት ነበረ። አይሁድ በዚያ ቀን ወደ መቃብር እንዲሄዱ አይፈቀድላቸውም ነበር። ስለዚህ ከሰንበት ቀን በኋላ በማለዳ ብዙ ሴቶች ሥጋው ላይ ተጨማሪ ሽቱ ለማርከፍከፍ ወደ ኢየሱስ መቃብር ሊሄዱ ተዘጋጁ።

OBS Image

በድንገትም ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ። እንደ መብረቅ የሚያበራ መልአክ ከሰማይ ታየ። የመቃብሩን መግቢያ ከድኖ የነበረውን ድንጋይ አንከባለለና ተቀመጠበት። መቃብሩን ይጠብቁ የነበሩት ወታደሮች ፈሩና እንደ ሞቱ ሰዎች ሆነው መሬት ላይ ወደቁ።

OBS Image

ሴቶቹ ወደ መቃብሩ በደረሱ ጊዜ መልአኩ፣ “አትፍሩ ኢየሱስ እዚህ የለም። ልክ እነሣለሁ ብሎ እንደ ተናገረው ከሙታን ተነሥቶአል! መቃብሩን ተመልከቱና እዩ” ብሎ ነገራቸው። ሴቶቹ ወደ መቃብሩ ውስጥ ተመለከቱና የኢየሱስን ሥጋ ያኖሩበትን ስፍራ ዐዩ። ሥጋው በዚያ አልነበረም!

OBS Image

ከዚያም መልአኩ ለሴቶቹ፣ “ሂዱና ‘ኢየሱስ ከሙታን ተነሥቶአል ቀድሞአችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው’” ብሎ ነገራቸው።

OBS Image

ሴቶቹ በፍርሃትና በታላቅ ደስታ ተሞልተው ነበር። የምሥራቹን ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር እየሮጡ ሄዱ።

OBS Image

ሴቶቹ የምሥራቹን ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር በመሄድ ላይ እያሉ፣ ኢየሱስ ታያቸው፣ እነርሱም ሰገዱለት። ኢየሱስ፣ “አትፍሩ። ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለደቀ መዛሙርቴ ንገሩአቸው። በዚያ ያዩኛል” አላቸው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 27፡62-28፡15፤ ማርቆስ 16፡1-11፤ ሉቃስ 24፡1-12፤ ዮሐንስ 20፡1-18።