am_obs/content/39.md

5.5 KiB

39. ኢየሱስ ለፍርድ ቀረበ

OBS Image

አሁን ጊዜው እኩለ ሌሊት ነው። ሊቀ ካህናቱ ይጠይቀው ዘንድ ወታደሮቹ ኢየሱስን ወደ ሊቀ ካህናቱ ቤት ወሰዱት። ጴጥሮስ ራቅ ብሎ ከኋላ ተከተላቸው። ኢየሱስን ወደ ቤቱ ባስገቡት ጊዜ፣ ጴጥሮስ በውጪ ሆኖ እሳት ይሞቅ ነበር።

OBS Image

በቤቱ ውስጥ የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስን ለፍርድ አቀረቡት። ስለ እርሱ የዋሹ ብዙ የሐሰት ምስክሮችን አመጡ። ይሁን እንጂ፣ ቃላቸው እርስ በርሱ አልተስማማም፣ ስለዚህ የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስ በማንኛውም ነገር በደለኛ መሆኑን ማረጋገጥ አልቻሉም።

OBS Image

በመጨረሻ፣ ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስን በቀጥታ ተመለከተውና፣ ንገረን፣ አንተ መሲሑ፣ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህን?" አለው።

OBS Image

ኢየሱስ፣ “እኔ ነኝ፣ እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር ተቀምጬና ከሰማይ ስመጣ ታያለህ” አለው። ሊቀ ካህናቱ በቊጣ ልብሱን ቀደደና ወደ ሌሎቹ የሃይማኖት መሪዎች፣ “ተጨማሪ ምስክሮች አያስፈልጉም! የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ሲል ሰምታችሁታል። ፍርዳችሁ ምንድን ነው?” ብሎ ጮኸ።

OBS Image

ሁሉም የአይሁድ መሪዎች፣ “መሞት ይገባዋል!” ብለው ለሊቀ ካህናቱ መለሱለት። ከዚያም ኢየሱስን ፊቱን ሸፈኑት፣ ተፉበት፣ መቱት፣ ዘበቱበትም።

OBS Image

ጴጥሮስ ከቤቱ ውጪ በመጠባበቅ ላይ እያለ የቤት ሠራተኛ የሆነች ልጅ ዐየችውና፣ “አንተም ደግሞ ከኢየሱስ ጋር ነበርክ!” አለችው። ጴጥሮስ እርስዋ የተናገረችውን ካደ። ከዚያ በኋላ ሌላዋ የቤት ሠራተኛ ያንኑ ተናገረች፣ ጴጥሮስም እንደገና ካደ። በመጨረሻ ሕዝቡ “ሁለታችሁም ከገሊላ ስለሆናችሁ አንተ ከኢየሱስ ጋር መሆንህን እናውቃለን” አሉ።

OBS Image

ከዚያም ጴጥሮስ፣ “ይህንን ሰው የማውቀው ከሆነ የእግዚአብሔር መርገም በእኔ ላይ ይሁን! ብሎ ማለ። ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ፣ ኢየሱስም ዘወር አለና ጴጥሮስን ተመለከተው።

OBS Image

ጴጥሮስ ሄደና በምሬት አለቀሰ። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ፣ የአይሁድ መሪዎች እንዲሞት በኢየሱስ ላይ እንደ ፈረዱበት ዐየ። ይሁዳ በሐዘን ተሞልቶ ሄደና ራሱን ገደለ።

OBS Image

በነጋታው ማለዳ ላይ የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስን ወደ ሮማው ገዥ ወደ ጲላጦስ አመጡት። ጲላጦስ ኢየሱስን ጥፋተኛ ነህ ብሎ ይፈርድበትና በሞት እንዲቀጣ ያደርጋል ብለው ተስፋ አደረጉ። ጲላጦስ ኢየሱስን፣ “የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው።

OBS Image

ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰለት፣ “አንተ አልህ፣ ነገር ግን መንግሥቴ ምድራዊ መንግሥት አይደለችም። እንደዚያ ብትሆን ኖሮ፣ አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር። ስለ እግዚአብሔር እውነቱን ለመናገር ወደ ምድር መጥቼአለሁ። እውነትን የሚወድ ሁሉ እኔን ይሰማኛል።” ጲላጦስ፣ “እውነት ምንድን ነው?” አለ።

OBS Image

ጲላጦስ ከኢየሱስ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ወደ ሕዝቡ ወጣና፣ “በዚህ ሰው ላይ ምንም በደል አላገኘሁበትም” አለ። የአይሁድ መሪዎችና ሕዝቡ ግን፣ “ስቀለው!” ብለው ጮኹ። ጲላጦስ፣ “በደለኛ አይደለም” ብሎ መለሰላቸው። እነርሱ ግን የበለጠ ጮኹ። ከዚያም ጲላጦስ ለሦስተኛ ጊዜ፣ “በደል የለበትም!” አለ።

OBS Image

ጲላጦስ ሕዝቡ መረበሽ ይጀምራሉ ብሎ ፈራ፣ ስለዚህ ኢየሱስን እንዲሰቅሉት ወታደሮቹን አዘዘ። የሮማ ወታደሮች ኢየሱስን ገረፉትና ቀይ ልብስ አለበሱት፣ እንዲሁም የሾኽ አክሊል በራሱ ላይ አደረጉ። ከዚያም፣ “እነሆ፣ የአይሁድ ንጉሥ!” በማለት ዘበቱበት።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 26፡57-27፡26፤ ማርቆስ 14፡53-15፡15፤ ሉቃስ 22፡54-23፡25፤ ዮሐንስ 18፡12-19፡16።