am_obs/content/38.md

7.2 KiB

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ

OBS Image

አይሁድ በያመቱ የፋሲካን በዓል ያከብሩ ነበር። ይህም በዓል ከብዙ ምእት ዓመታት በፊት እግዚአብሔር ቅድማያቶቻቸውን በግብፅ ከነበረው ባርነት እንዴት እንዳዳናቸው የሚከበር ነበር። ኢየሱስ መጀመሪያ በይፋ መስበኩንና ማስተማሩን ከጀመረ ከሦስት ዓመት ገደማ በኋላ፣ ይህን ፋሲካ በኢየሩሳሌም ከእነርሱ ጋር ሊያከብር እንደ ፈለገ፣ በዚያም እንደሚገደል ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው።

OBS Image

ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ይሁዳ ተብሎ የሚጠራ ሰው ነበር። ይሁዳ የሐዋርያቱ የገንዘብ ከረጢት ኃላፊ ነበር፣ ነገር ግን ገንዘብ ይወድ ነበርና ብዙ ጊዜ ከከረጢቱ ውስጥ ገንዘብ ይሰርቅ ነበር። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም ከደረሱ በኋላ፣ ይሁዳ ወደ አይሁድ መሪዎች ሄደና ኢየሱስን በገንዘብ አሳልፎ ሊሰጣቸው ተስማማ። ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የአይሁድ መሪዎች እንደ ካዱና ሊገድሉት ያሤሩ እንደ ነበር ዐወቀ።

OBS Image

የአይሁድ መሪዎች በሊቀ ካህናቱ እየተመሩ፣ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ለይሁዳ ሠላሳ ብር ከፈሉት። ልክ ነቢያት እንደ ተነበዩት ይህ ሆነ። ይሁዳ ተስማማ፣ ገንዘቡንም ይዞ ሄደ። ኢየሱስን እንዲይዙት ሊረዳቸው አጋጣሚ መፈለግ ጀመረ።

OBS Image

በኢየሩሳሌም፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ፋሲካን አከበረ። በፋሲካው ምግብ ጊዜ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ቈረሰ። እንዲህም አለ፣ “እንካችሁ ይህንን ብሉ። ይህ ስለ እናንተ የተሰጠ ሥጋዬ ነው። ይህንን ለመታሰቢያዬ አድርጉት።” በዚህ ዓይነት ኢየሱስ ሥጋው ስለ እርሱ እንደሚሠዋ ነገራቸው።

OBS Image

ከዚያም ኢየሱስ ጽዋን አንሣና፣ “ይህንን ጠጡ። ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የዐዲስ ኪዳን ደሜ ነው። ይህንን በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ለመታሰቢያዬ አድርጉት።”

OBS Image

ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ ደነገጡ፣ እንዲህ ያለ ነገር ማን ያደርጋል ብለውም ጠየቁ። ኢየሱስ፣ “ይህንን ቊራሽ እንጀራ የምሰጠው ሰው እኔን አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ። ከዚያ በኋላ እንጀራውን ለይሁዳ ሰጠው።

OBS Image

ይሁዳ እንጀራውን ከተቀበለ በኋላ፣ ሰይጣን ገባበት። ይሁዳ ኢየሱስን እንዲይዙ የአይሁድ መሪዎችን ሊረዳቸው ሄደ። ጊዜው ማታ ነበር።

OBS Image

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እራት ከበሉ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ሄዱ። ኢየሱስ፣ “ዛሬ ማታ ሁላችሁም ትተዉኛላችሁ። ‘እረኛውን እመታለሁ በጎቹም ሁሉ ይበተናሉ’ ተብሎ ተጽፎአል” አለ።

OBS Image

ጴጥሮስ፣ “ሌሎቹ ሁሉ ቢተዉህ እንኳ፣ እኔ ግን አላደርገውም!” ብሎ መለሰ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፣ “ሰይጣን ሁላችሁንም ሊወስዳችሁ ይፈልጋል፣ ነገር ግን ጴጥሮስ እምነትህ እንዳይደክም ጸልዬልሃለሁ። እንደዚያም ሆኖ ግን ዛሬ ማታ ዶሮ ከመጮኹ በፊት እንደማታውቀኝ እንኳ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ።”

OBS Image

በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስ፣ “መሞት ቢኖርብኝ እንኳ፣ ከቶ አልክድህም” አለው። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ሁሉ ይህንኑ አሉ።

OBS Image

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ቦታ ሄደ። ኢየሱስ ወደ ፈተና እንዳይገቡ እንዲጸልዩ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። ከዚያም ኢየሱስ ብቻውን ሊጸልይ ሄደ።

OBS Image

ኢየሱስ ሦስት ጊዜ ጸለየ፣ “አባቴ ሆይ፣ ቢቻልስ ይህን የመከራ ጽዋ እንዳልጠጣው አድርግ። ነገር ግን የሰዎች ኃጢአት ይቅር የሚባልበት ሌላ መንገድ ከሌለ፣ ፈቃድህ ይሁን።” ኢየሱስ በጣም ታወከ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ። እግዚአብሔር ሊያበረታታው መልአክ ላከ።

OBS Image

ከእያንዳንዱ የጸሎት ጊዜ በኋላ ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመላለሰ፣ እነርሱ ግን ተኝተው ነበር። ሦስተኛ በተመለሰ ጊዜ ግን፣ “ተነሡ! አሳልፎ የሚሰጠኝ እዚህ ነው” አለ።

OBS Image

ይሁዳ ከአይሁድ መሪዎች፣ ከወታደሮችና ከብዙ ሕዝብ ጋር መጣ። ሰይፍና ዱላ ይዘው ነበር። ይሁዳ ወደ ኢየሱስ መጣና፣ “መምህር ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን” አለው፣ ሳመውም። ይህም የአይሁድ መሪዎች ማንን እንደሚይዙ ምልክት ነበር። ከዚያም ኢየሱስ፣ “ይሁዳ፣ በመሳም አሳልፈህ ትሰጠኛለህን?” አለ።

OBS Image

ወታደሮቹ ኢየሱስን እንደ ያዙት፣ ጴጥሮስ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ጆሮ ቈረጠ። ኢየሱስ፣ “ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ! ይከላከሉልኝ ዘንድ የመላእክት ሠራዊት እንዲልክልኝ አባቴን መጠየቅ እችላለሁ” አለው። ከዚያም ኢየሱስ የሰውዬውን ጆሮ ፈወሰው። ኢየሱስ ከተያዘ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ሸሹ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 26፡14-56፤ ማርቆስ 14፡10-50፤ ሉቃስ 22፡1-53፤ ዮሐንስ 12፡6፤ 18፡1-11።