am_obs/content/37.md

4.9 KiB

37. ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት አስነሣ

OBS Image

አንድ ቀን ኢየሱስ አልዓዛር በጣም ታሞአል የሚል መልእክት ደረሰው። አልዓዛርና ሁለቱ እኅቶቹ ማርያምና ማርታ የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች ነበሩ። ኢየሱስ ይህንን ወሬ በሰማ ጊዜ፣ “ይህ ሕመም ለእግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም” አለ። ኢየሱስ ወዳጆቹን ይወዳቸው ነበር፣ ነገር ግን ለሁለት ቀናት በነበረበት ስፍራ ቆየ።

OBS Image

ሁለቱ ቀናት ካለፉ በኋላ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ወደ ይሁዳ እንሂድ” አላቸው። “ነገር ግን መምህር ሆይ፣”ልክ ከጥቂት ጊዜ በፊት በዚያ ያሉት ሕዝብ ሊገድሉህ ይፈልጉ ነበር!" ብለው ደቀ መዛሙርቱ መለሱለት። ኢየሱስ፣ “ወዳጃችን አልዓዛር አንቀላፍቶአል፣ ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አላቸው።

OBS Image

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት፣ “ጌታ ሆይ፣ አልዓዛር ተኝቶስ ከሆነ፣ ይድናል” ብለው መለሱለት። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በግልጽ ነገራቸው፣ “አልዓዛር ሞቶአል። እናንተ በእኔ ታምኑ ዘንድ እዚያ ባለመኖሬ ደስ ብሎኛል።”

OBS Image

ኢየሱስ አልዓዛር ወደ ተወለደበት ከተማ በደረሰ ጊዜ፣ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን ሆኖት ነበር። ማርታ ኢየሱስን ልትገናኘው ወጣችና እንዲህ አለች፣ “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትኖር ኖሮ ወንድሜ አይሞትም ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እንደሚሰጥህ አምናለሁ።”

OBS Image

ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰላት፣ “እኔ ትንሣኤና ሕይወት ነኝ። በእኔ የሚያምን ሁሉ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል። በእኔ የሚያምን ሁሉ ከቶ አይሞትም። ይህን ታምኛለሽን? ማርታ፣”አዎን፣ ጌታ ሆይ! አንተ መሲሑ፣ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ" ብላ መለሰችለት።

OBS Image

ከዚያም ማርያም መጣች። በኢየሱስ እግር ወደቀችና፣ “ጌታ ሆይ፣ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለች። ኢየሱስ፣ “አልዓዛርን ወዴት ነው ያኖራችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው። “በመቃብር ነው። ናና እይ” ብለው ነገሩት። ከዚያም ኢየሱስ አለቀሰ።

OBS Image

መቃብሩ ዋሻ ነበር፣ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። ኢየሱስ ወደ መቃብሩ በደረሰ ጊዜ ድንጋዩን አንከባሉት" ብሎ ነገራቸው። ነገር ግን ማርታ፣ “ከሞተ አራት ቀን ሆኖታል። አሁን ይሸታል” አለችው።

OBS Image

ኢየሱስ፣ “በእኔ ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርኩሽምን?” አላት። ስለዚህ ድንጋዩን አንከባለሉት።

OBS Image

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ወደ ላይ ተመለከተና፣ “አባት ሆይ፣ ስለምትሰማኝ አመሰግንሃለሁ። አንተ ሁልጊዜ እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፣ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ እዚህ ስለ ቆሙት ስለ እነዚህ ሰዎች ሁሉ ይህን እላለሁ” አለ። ከዚያም ኢየሱስ፣ “አልዓዛር ሆይ፣ ወደ ውጭ ና!” ብሎ ጮኸ።

OBS Image

ስለዚህ አልዓዛር ወጣ! በከፈን እንደ ተገነዘ ነበር። ኢየሱስም፣ “ፍቱትና ይሂድ ተዉት!” አላቸው። ከአይሁድ ብዙዎች በዚህ ተአምር ምክንያት በኢየሱስ አመኑ።

OBS Image

ነገር ግን የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ቀኑ፣ ስለዚህ ኢየሱስንና አልዓዛርን እንዴት መግደል እንዳለባቸው ለማቀድ በአንድ ላይ ተሰበሰቡ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዮሐንስ 11፡1-46።