am_obs/content/36.md

2.7 KiB

36. የኢየሱስ መልክ ተለወጠ

OBS Image

አንድ ቀን ኢየሱስ ሦስቱን ደቀ መዛሙርቱን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ያዞ ሊጸልዩ ወደ ረጅም ተራራ ወጡ። ( ዮሐንስ የተባለው ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ያጠመቀው ሰው አልነበረም።)

OBS Image

ኢየሱስ በመጸለይ ላይ እያለ፣ ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፣ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ፣ በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ሰው ሊያነጻው እስከማይችል ድረስ በጣም ነጭ ሆነ።

OBS Image

በዚያን ጊዜ ሙሴና ነቢዩ ኤልያስ ታዩ። እነዚህ ሰዎች በመቶዎች ከሚቈጠሩ ዓመታት በፊት በምድር ላይ ይኖሩ ነበር። በቅርቡ በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው ሞቱ ከኢየሱስ ጋር ተነጋገሩ።

OBS Image

ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር በመነጋገር ላይ እያሉ ጴጥሮስ ኢየሱስን፣ “በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው። አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ እንዲሁም አንድ ለኤልያስ፣ ሦስት መጠለያዎችን እንሥራ” አለው። ጴጥሮስ የሚናገረውን አያውቅም ነበር።

OBS Image

ጴጥሮስ እየተናገረ እያለ፣ ብሩህ ደመና መጥቶ ከበባቸውና ከደመናው ድምፅ፣ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፣ እርሱን ስሙት” አለ። ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ፈሩና መሬት ላይ ወደቁ።

OBS Image

ያኔ ኢየሱስ ዳሰሳቸውና፣ “አትፍሩ፣ ተነሡ” አላቸው። ዙሪያቸውን ሲያዩ ከኢየሱስ በቀር ማንም አልነበረም።

OBS Image

ኢየሱስና ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ከተራራው ወረዱ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፣ “በዚህ ስለ ሆነው ነገር ገና ለማንም አትናገሩ። እኔ በቶሎ እሞታለሁ፣ ሕያውም እሆናለሁ። ከዚያ በኋላ ለሰዎች መናገር ትችላላችሁ።”

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 17፡1-9፤ ማርቆስ 9፡2-8፤ ሉቃስ 9፡28-36።