am_obs/content/35.md

4.9 KiB
Raw Permalink Blame History

35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ

OBS Image

አንድ ቀን ኢየሱስ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችንና ሊሰሙት የተሰበሰቡ ሌሎች ኃጢአተኞችን ያስተምር ነበር።

OBS Image

ደግሞም በዚያ የነበሩ አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ወዳጆች አድርጎ ሲቀበላቸው ዐዩ፣ እርስ በርሳቸውም ይነቅፉት ጀመር። ስለዚህ ኢየሱስ ይህንን ታሪክ ነገራቸው።

OBS Image

ሁለት ልጆች ያሉት አንድ ሰው ነበር። ታናሹ ልጅ አባቱን፣ አባቴ ሆይ፣ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል አሁን ስጠኝ! አለው። ስለዚህ አባትዬው ገንዘቡን ለሁለቱ ልጆቹ አካፈላቸው።"

OBS Image

“ታናሹ ልጅ ወዲያውኑ ያለውን ሁሉ ሰበሰበና ሩቅ አገር ሄዶ በኃጢአት እየኖረ ገንዘቡን አጠፋ።

OBS Image

“ከዚያ በኋላ ታናሹ ልጅ በነበረበት አገር ጽኑ ረሀብ ሆነ፣ ምግብ የሚገዛበት ገንዘብም አልነበረውም። ስለዚህ ብቸኛ የነበረውን፣ እሪያዎችን የመመገብ ሥራ ያዘ። በጣም ተጐሳቊሎና ተርቦ ስለ ነበር የእሪያዎችን ምግብ ለመብላት ይመኝ ነበር።”

OBS Image

“በመጨረሻ፣ ታናሹ ልጅ ለራሱ እንዲህ አለ፣ ‘ምን እያደረግሁ ነው? የአባቴ አገልጋዮች ሁሉ የሚበሉት ብዙ ምግብ አላቸው፣ እኔ ግን ተርቤአለሁ። ወደ አባቴ ተመልሾ እሄድና ከአገልጋዮቹ አንዱ እንዲያደርገኝ እለምነዋለሁ።’”

OBS Image

ስለዚህ ታናሹ ልጅ ወደ አባቱ ቤት መመለስ ጀመረ። ገና በሩቅ እያለ አባቱ ዐየውና አዘነለት። ወደ ልጁ ሮጠና አቀፈው ሳመውም።"

OBS Image

“ልጁም አለ፣ ‘አባቴ ሆይ፣ እግዚአብሔርንና አንተን በድዬአለሁ። ልጅህ ልባል አይገባም።’”

OBS Image

“ነገር ግን አባቱ ከአገልጋዮቹ ለአንዱ እንዲህ ብሎ ነገረው፣ ‘ፈጥነህ ሂድና ማለፊያ ልብስ አምጥተህ ለልጄ አልብሰው! ለጣቱ ቀለበት ለእግሩም ጫማ አድርግለት። ከዚያም እንበላና ደስ ይለን ዘንድ የሰባ ፍሪዳ አምጥታችሁ እረዱ፣ ምክንያቱም ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፣ ሕያውም ሆኖአል! ጠፍቶ ነበር፣ አሁን ግን ተገኝቶአል!’”

OBS Image

“ስለዚህ ሰዎቹ ደስ ይላቸው ጀመር። ብዙ ሳይቆይ፣ ይሠራበት ከነበረው እርሻ ታላቅ ወንድሙ ወደ ቤት መጣ። የሙዚቃና የዘፈን ድምፅ ሰማ፣ ምን እየሆነ ነው ብሎም ተገረመ።”

OBS Image

“ታላቁ ልጅ ወንድሙ ስለ መጣ እየተደሰቱ መሆናቸውን ባወቀ ጊዜ፣ በጣም ስለ ተቈጣ ወደ ቤት ለመግባት ፈቃደኛ አልሆነም። አባቱ ወጣና ገብቶ ከእነርሱ ጋር እንዲደሰት ለመነው፣ እርሱ ግን እምቢ አለ።”

OBS Image

ታላቁ ልጅ አባቱን እንዲህ አለው፣ ‘በእነዚህ ዓመታት ሁሉ በታማኝነት ለአንተ ሠርቼአለሁ! ከቶ ትእዛዝህን አልተላለፍኩም፣ እስካሁንም ከጓደኞቼ ጋር እንድደሰት አንድ ጥቦት ፍየል እንኳ አልሰጠኸኝም። ኃጢአት በመሥራት ገንዘብህን ያጠፋው ይህ ልጅህ ግን ወደ ቤት በመጣ ጊዜ፣ የሰባ ፍሪዳ አረድህለት!"

OBS Image

“አባቱ እንዲህ ብሎ መለሰለት፣ ‘ልጄ፣ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፣ ያለኝም ነገር ሁሉ የአንተ ነው። መደሰታችን ግን ትክክል ነው፣ ምክንያቱም ወንድምህ ሞቶ ነበር፣ አሁን ግን ሕያው ሆኖአል። ጠፍቶ ነበር፣ አሁን ግን ተገኝቶአል!”

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሉቃስ 15፡11-32።