am_obs/content/33.md

3.2 KiB

33. የአርሶ አደሩ ታሪክ

OBS Image

አንድ ቀን ኢየሱስ በሐይቁ ዳርቻ አጠገብ በጣም ብዙ ሕዝብ እያስተማረ ነበር። ኢየሱስ ሊናገራቸው በቂ ቦታ ለማግኘት በውሃው ዳርቻ በጀልባ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ በጣም ብዙ ሰዎች ሊሰሙት መጡ። በጀልባው ተቀመጠና ሕዝቡን አስተማረ።

OBS Image

ኢየሱስ ይህንን ታሪክ ተናገረ። “አንድ አርሶ አደር ዘር ሊዘራ ወጣ። በእጁ ዘሩን ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፣ ወፎችም መጥተው ያን ዘር በሙሉ በሉት።”

OBS Image

“ሌላው ዘር ብዙ መሬት በሌለበት በአለታማ መሬት ላይ ወደቀ፣ ነገር ግን ሥሩ ወደ መሬት መጥለቅ አልቻለም። ፀሐይዋ በወጣችና በሞቀች ጊዜ፣ ቡቃያው ጠወለገና ደረቀ።”

OBS Image

“አሁንም ሌላው ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ። ይህ ዘር መብቀል ጀመረ፣ ነገር ግን እሾኹ አነቀው። ስለዚህ በእሾኻማው መሬት ላይ የበቀለው ቡቃያ ምንም ፍሬ አላፈራም።”

OBS Image

“ሌላው ዘር በመልካም መሬት ላይ ወደቀ። ይህ ዘር በቀለና አንዱ 30፣ አንዱ 60፣ አንዱም መቶ ፍሬ ሰጠ። ጆሮ ያለው ይስማ!”

OBS Image

ይህ ታሪክ ደቀ መዛሙርቱን ግራ አጋባቸው። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ አብራራላቸው፣ “ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። የመንገዱ ዳር የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ ሰው ነው፣ ነገር ግን አያስተውለውም፣ ዲያብሎስም ቃሉን ይወስድበታል።”

OBS Image

“በአለታማ መሬት የተዘራው ዘር የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ በደስታ የሚቀበለው ሰው ነው። ነገር ግን መከራ ወይም ስደት በሚያጋጥመው ጊዜ እምነቱን ይተዋል።”

OBS Image

“እሾኻማው መሬት የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ ሰው ነው፣ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ የዚህ ዓለም ዐሳብ፣ ባለጠግነትና ደስታ ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር ያንቃል። ከዚህ የተነሣ፣ የሰማው ትምህርት ፍሬ አያፈራም።

OBS Image

“መልካሙ መሬት ግን የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፣ የሚያምነውና ፍሬ የሚያፈራ ሰው ነው።”

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 13፡1-8፣ 18-23፤ ማርቆስ 4፡1-8፣ 13-20፤ ሉቃስ 8፡4-15።