am_obs/content/27.md

4.2 KiB

27.የደጉ ሳምራዊ ታሪክ

OBS Image

አንድ ቀን አንድ የአይሁድ ሕግ ዐዋቂ ሊፈትነው ወደ ኢየሱስ መጣ፣ “መምህር ሆይ፣ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” አለው። ኢየሱስ፣ “በእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈው ምንድን ነው?” ብሎ መለሰለት።

OBS Image

ሕግ ዐዋቂው የእግዚአብሔርሕግ፣ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም ዐሳብህም ውደድ። ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ” ይላል ብሎ መለሰ። ኢየሱስ፣ “ትክክል ነህ! ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ” አለው።

OBS Image

ነገር ግን ሕግ ዐዋቂው ጻድቅ መሆኑን ለማረጋገጥ ፈለገ፣ ስለዚህ፣ “ባልንጀራዬ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀ።

OBS Image

ኢየሱስ ታሪክ በመናገር ለሕግ ዐዋቂው መለሰለት። “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ይጓዝ የነበረ አንድ አይሁዳዊ ነበረ።”

OBS Image

“ሰውዬው በመጓዝ ላይ እያለ ወንበዴዎች ያዙት። የነበረውን ነገር ሁሉ ወሰዱበትና እስኪሞት ድረስ ደበደቡት። ከዚያም ሄዱ።”

OBS Image

ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ አንድ አይሁዳዊ ካህን በዚያ መንገድ ይጓዝ ነበር። ይህ የሃይማኖት መሪ የተዘረፈውንና የተደበደበውን ሰው ባየ ጊዜ ወደ መንገዱ ሌላኛ ጎን ሄደ፣ ርዳታ የፈለገውን ሰው ቸል አለውና ጕዞውን ቀጠለ።"

OBS Image

ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣አንድ ሌዋዊ መጣ።( ሌዋውያን በቤተ መቅደስ ካህናቱን የሚረዱ የአይሁድ ነገድ ነበሩ።) ሌዋዊውም ደግሞ ወደ መንገዱ ሌላኛ ጎን ተሻገረና የተዘረፈውንና የተደበደበውን ሰው በቸልታ አለፈው።"

OBS Image

በዚያ መንገድ የወረደው የሚቀጥለው ሰው ሳምራዊ ነበር።(ሳምራውያን የሌሎች አገሮች ሰዎችን ያገቡ የአይሁድ ዝርያዎች ነበሩ።ሳምራውያንና አይሁዳውያን እርስ በርስ ይጠላሉ ነበር።) ነገር ግን ሳምራዊው አይሁዳዊውን ባየ ጊዜ በጣም አድርጎ ራራለት። ስለዚህ ተንከባከበውና ቊስሉን አሰረለት።"

OBS Image

“ከዚያ በኋላ ሳምራዊው ሰውዬውን አንሥቶ በራሱ አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደሪያ ወሰደው ተንከባከበውም።”

OBS Image

“በማግሥቱም ሳምራዊው ጕዞውን መቀጠል አስፈለገው። ለእንግዶች ማረፊያው ባለቤት ጥቂት ገንዘብ ሰጠውና፣”ተንከባከበው፣ ከዚህ ሌላ ገንዘብ የምታወጣ ከሆነ በምመለስበት ጊዜ እከፍልሃለሁ አለው።"

OBS Image

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ሕግ ዐዋቂውን፣ “ምን ታስባለህ? ለተዘረፈውና ለተደበደበው ሰው ባልንጀራው ከሦስቱ ሰዎች የትኛው ነበር?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፣ “ምሕረት ያደረገለት ነበር” ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ፣ “አንተም ሄደህ እንደዚሁ አድርግ” ብሎ ነገረው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሉቃስ 10፡25-37።