am_obs/content/23.md

4.5 KiB

23. የኢየሱስ ልደት

OBS Image

ማርያም ዮሴፍ ለተባለ ጻድቅ ሰው ታጭታ ነበር። እጮኛዋ ዮሴፍ ማርያም መፀነስዋን በሰማ ጊዜ፣ ሕፃኑ የእርሱ እንዳልሆነ ዐወቀ። ማርያምን ለማሳፈር አልፈለገም፣ ስለዚህ ዝም ብሎ ሊፈታት ዐሰበ። ያንን ከማድረጉ በፊት መልአክ መጣና በሕልም ተናገረው።

OBS Image

መልአኩ እንዲህ አለ፡- “ዮሴፍ፣ ማርያምን ሚስት አድርገህ ለመውሰድ አትፍራ። በውስጥዋ ያለው ሕፃን ከመንፈስ ቅዱስ ነው። ወንድ ልጅ ትወልዳለች። ስሙን ኢየሱስ ብለህ ጥራው (ትርጕሙም፣ ‘ያሕዌ ያድናል’ ማለት ነው)፣ ምክንያቱም ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል።”

OBS Image

ስለዚህ ዮሴፍ ማርያምን አገባትና ሚስቱ አድርጎ ወደ ቤቱ ወሰዳት፣ ነገር ግን እስክትወልድ ድረስ ከእርስዋ ጋር አልተኛም።

OBS Image

ማርያም የምትወልድበት ጊዜ እንደ ደረሰ፣ የሮማ መንግሥት ሁሉም ሰው ለቈጠራ ቅድማያቶቹ ወደ ኖሩበት ከተማ እንዲሄድ ተናገረ። ዮሴፍና ማርያም ከሚኖሩበት ከናዝሬት ወደ ቤተ ልሔም ረጅም ጕዞ ተጓዙ ምክንያቱም በቤተ ልሔም ከተማ የተወለደው ቅድማያታቸው ዳዊት ነበረ።

OBS Image

ወደ ቤተ ልሔም በደረሱ ጊዜ ማረፊያ ስፍራ አልነበረም። ሊያገኙ የቻሉት ብቸኛ ክፍል እንስሶች የሚያድሩበት ስፍራ ነበረ። ሕፃኑ በተወለደ ጊዜ የሚያስተኙበት አልጋ ስላልነበረ እናቱ በከብቶች መመገቢያ ገንዳ አስተኛችው። ስሙንም ኢየሱስ አሉት።

OBS Image

በዚያ ሌሊት በአቅራቢያው ባለ ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን የሚጠብቁ ጥቂት እረኞች ነበሩ። በድንገት የሚያበራ መልአክ ታያቸው፣ እነርሱም ፈሩ። መልአኩ፣ “አትፍሩ፣ ምክንያቱም ለእናንተ የምሥራች አለኝ። መሲሑ፣ ጌታ በቤተልሔም ተወልዶአል!” አለ።

OBS Image

“ሄዳችሁ ሕፃኑን ፈልጉ፣ በጨርቅ ተጠቅልሎና በእንስሶች መመገቢያ ገንዳ ተኝቶ ታገኙታላችሁ።” ድንገትም ሰማያት በመላእክት ተሞሉ፣ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ “ክብር ለእግዚአብሔር በሰማይ ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ!” አሉ።

OBS Image

እረኞች ኢየሱስ ወደ ነበረበት ስፍራ ፈጥነው ደረሱና ልክ መልአኩ እንደ ነገራቸው በእንስሶች መመገቢያ ገንዳ ተኝቶ አገኙት። በጣም ደስ አላቸው። ማርያምም ደግሞ በጣም ደስ አላት። እረኞቹ ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፣ በጎቻቸው ወደ ነበሩባቸው ሜዳዎች ተመለሱ።

OBS Image

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከሩቅ ምሥራቅ አገሮች የሆኑ ጠቢባን በሰማይ አንድ ያልተለመደ ኮከብ ዐዩ። ዐዲስ የአይሁድ ንጉሥ የተወለደ መሆኑን እንደሚያመለክት ተገነዘቡ። ስለዚህ ይህንን ንጉሥ ለማየት በጣም ረጅም ርቀት ተጓዙ። ወደ ቤተ ልሔም መጡና ኢየሱስና ወላጆቹ የነበሩበትን ቤት አገኙት።

OBS Image

ጠቢባኑ ኢየሱስን ከእናቱ ጋር ባዩት ጊዜ ወድቀው ሰገዱለት። ለኢየሱስ ውድ ስጦታዎች ሰጡት። ከዚያም ወደ አገራቸው ተመለሱ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 1፤ ሉቃስ 2።