am_obs/content/20.md

6.6 KiB

20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ

OBS Image

የእስራኤል መንግሥትና የይሁዳ መንግሥት ሁለቱም በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠሩ። እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋርበሲና ተራራ ያደረገውን ቃልኪዳን አፈረሱ። እግዚአብሔርንስሐ እንዲገቡና እንደገና እንዲያመልኩት ሊያስጠነቅቃቸው ነቢያቱንላከ፣ እነርሱ ግን አንታዘዝም አሉ።

OBS Image

ስለዚህ እግዚአብሔር ጠላቶቻቸው እንዲያጠፉአቸው በመፍቀድ ሁለቱንም መንግሥታት ቀጣቸው። የኃያልዋ፣ የጨካኝዋ አገር የአሦር ንጉሠ ነገሥት ግዛት የእስራኤልን መንግሥት አጠፋች፣ ዋጋ ያለውን ነገር ሁሉ ወሰደች፣ ከአገሪቱ አብዛኛውንም አቃጠለች።

OBS Image

አሦርያውያን መሪዎችን፣ ሀብታሞችን፣ እንዲሁም ሙያ የነበራቸውን ሰዎች ሁሉ ሰበሰቡና ወደ አሦር ወሰዱአቸው። ያልተገደሉት በጣም ድሆች የነበሩት እስራኤላውያን ብቻ በእስራኤል መንግሥት ቀሩ።

OBS Image

ከዚያም አሦራውያን የእስራኤል መንግሥት በነበረባት ምድር እንዲኖሩ ባዕዳንን አመጡ። ባዕዳኑ የፈረሱትን ከተሞች እንደገና ሠሩና በዚያ ቀርተው የነበሩትን እስራኤላውያን አገቡ። ባዕዳንን ያገቡት የእስራኤላውያን ዝርያዎች ሳምራውያን ተብለው ይጠሩ ነበር።

OBS Image

የእስራኤል መንግሥት ሕዝብ እግዚአብሔርን ስላላመኑበትና ስላልታዘዙት እንዴት እንደ ቀጣቸው በይሁዳ መንግሥት የነበሩት ሕዝብ ዐዩ። እንደዚያም ሆኖ ግን የይሁዳ መንግሥት ሕዝብ የከነዓናውያንን አማልክት ጨምሮ ጣዖታትን አመለኩ። እግዚአብሔርም እንዲያስጠነቅቁአቸው ነቢያትን ላከ፣ እነርሱ ግን አንሰማም አሉ።

OBS Image

አሦራውያን የእስራኤልን መንግሥት ካጠፉ ከ100 ዓመታት ገደማ በኋላ የይሁዳን መንግሥት እንዲወጉ እግዚአብሔር ባቢሎናውያንን ላከ። ባቢሎን ኃያል የንጉሠ ነገሥት ግዛት ነበረች። የይሁዳ ንጉሥ የናቡከደነፆር አገልጋይ ለመሆንና በያመቱ ብዙ ገንዘብ ሊከፍለው ተስማማ።

OBS Image

ነገር ግን ከጥቂት ዓመታት በኋላ የይሁዳ ንጉሥ በባቢሎን ላይ ዓመፀ። ስለዚህ ባቢሎናውያን ተመልሰው መጥተው የይሁዳን መንግሥት ወጉ። የኢየሩሳሌምን ከተማ ያዙ፣ ቤተ መቅደሱን አጠፉ፣ እንዲሁም የከተማይቱንና የቤተ መቅደሱን መዛግብት ሁሉ ወሰዱ።

OBS Image

የይሁዳ ንጉሥ ስላመፀበት ሊቀጣው የናቡከደነፆር ወታደሮች የይሁዳን ንጉሥ ወንድ ልጆች በፊቱ ገደሉ፤ እርሱንም ዓይኖቹን አሳወሩ። ከዚያ በኋላ በባቢሎን በእስር ቤት እንዲሞት ንጉሡን ወሰዱት።

OBS Image

ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ በእርሻ እንዲሠሩ እጅግ በጣም ድሆች የሆኑትን ሰዎች ብቻ በመተው ከሞላ ጐደል የይሁዳን መንግሥት ሕዝብ ሁሉ ወደ ባቢሎን ማርከው ወሰዱ። የእግዚአብሔር ሕዝብ የተስፋዪቱን ምድር እንዲለቁ የተገደዱበት ይህ ወቅት ምርኮ ተብሎ ይጠራል።

OBS Image

ምንም እንኳ እግዚአብሔር ወደ ምርኮ በመውሰድ ሕዝቡን ስለ ኃጢአታቸው ቢቀጣቸውም እነርሱንና ተስፋዎቹን አልረሳም። እግዚአብሔር ሕዝቡን መጠበቁንና በነቢያቱ በኩል እነርሱን ማነጋገሩን ቀጠለ። ከሰባ ዓመት በኋላ፣ ወደ ተስፋዪቱ ምድር እንደ ገና እንዲመለሱ ተስፋ ሰጠ።

OBS Image

ከሰባ ዓመታት ገደማ በኋላ፣ የፋርስ ንጉሥ ባቢሎንን አሸነፈ፣ ስለዚህ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ግዛት የባቢሎንን ንጉሠ ነገሥት ግዛት ተካ። አሁን እስራኤላውያን አይሁዶች ተብለው ተጠሩ አብዛኞቻቸውም ሕይወታቸውን በሙሉ በባቢሎን የኖሩ ነበሩ። በጣም ያረጁ ጥቂት አይሁዶች ብቻ የይሁዳን ምድር አስታወሱ።

OBS Image

የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ግዛት ጠንካራ ነገር ግን ለያዛቸው ሕዝብ መሐሪ ነበር። ቂሮስ የፋርሳውያን ንጉሥ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ወደ ይሁዳ መመለስ የፈለገ ማንኛውም አይሁዳዊ ፋርስን ለቆ ወደ ይሁዳ መመለስ እንደሚችል ትእዛዝ ሰጠ። ቤተ መቅደሱን እንደገና እንዲሠሩ የገንዘብ ድጋፍ ሳይቀር አደረገላቸው! ስለዚህ በምርኮ ከቆዩባቸው ሰባ ዓመታት በኋላ፣ ጥቂት የአይሁዶች ቡድን በይሁዳ ወዳለችው ኢየሩሳሌም ከተማ ተመለሱ።

OBS Image

ሕዝቡ ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ፣ ቤተ መቅደሱንና በከተማዪቱ ዙሪያ ያለውን ቅጥር እንደ ገና ሠሩ። ምንም እንኳ እስካሁን ድረስ በሌሎች ሕዝቦች የተገዙ ቢሆኑም፣ ዳግመኛ በተስፋዪቱ ምድር ኖሩና በቤተ መቅደሱ አመለኩ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከ2ኛ ነገሥት 17፤ 24-25፤ 2ኛ ዜና 36፤ ዕዝራ 1-10፤ ነህምያ 1-13።