am_obs/content/19.md

8.9 KiB

19. ነቢያቱ

OBS Image

እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ታሪክ በሙሉ፣ ነቢያትን ላከላቸው። ከእግዚአብሔር መልእክት ሰሙ ከዚያም የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ ነገሩአቸው።

OBS Image

አክአብ በእስራኤል መንግሥት ላይ በነገሠ ጊዜ ኤልያስ ነቢይ ነበረ። አክዓብ በኣል ተብሎ የሚጠራ የሐሰት አምላክ እንዲያመልኩ ሕዝቡን ያደፋፈረ ክፉ ሰው ነበር። ኤልያስ ለአክዓብ፣ “እኔ እስከምናገር ድረስ በእስራኤል ዝናብ ወይም ጠል አይኖርም” አለው። ይህ አክዓብን በጣም አስቈጣው።

OBS Image

እግዚአብሔር ሊገድለው ከሚፈልገው ከአክዓብ ለመሸሸግ በምድረ በዳ ወዳለ ወንዝ እንዲሄድ ለኤልያስ ነገረው። በየጠዋቱና በየምሽቱ ወፎች እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር። አክዓብና ጦር ሠራዊቱ ኤልያስን ፈለጉት፣ ነገር ግን ሊያገኙት አልቻሉም። ድርቁ በጣም ከባድ ነበርና በመጨረሻ ወንዙ ደረቀ።

OBS Image

ስለዚህ ኤልያስ ወደ አንድ ጐረቤት አገር ሄደ። በዚያች አገር በረሀቡ ምክንያት አንዲት መበለትና ወንድ ልጅዋ ምግብ ሊያልቅባቸው ተቃርበው ነበር። ነገር ግን ኤልያስን ተንከባከቡት፣ እግዚአብሔርም ዱቄቱ ከማድጋ ዘይቱም ከማሰሮ እንዳይጐድል አድርጎ መገባቸው። በረሀቡ ጊዜ ሁሉ ምግብ ነበራቸው። ኤልያስ በዚያ ለአያሌ ዓመታት ተቀመጠ።

OBS Image

ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ዝናብ የሚያዘንብ መሆኑን ወደ እስራኤል መንግሥት ተመልሶ ለአክዓብ እንዲነግረው እግዚአብሔር ለኤልያስ ነገረው። አክዓብ ኤልያስን ባየው ጊዜ፣ “አንተ ችግር ፈጣሪ፣ መጣህ አይደል!” አለው። ኤልያስ እንዲህ ብሎ መለሰት፣ “ችግር ፈጣሪ አንተ ነህ! እውነተኛውን አምላክ፣ ያህዌን ትተሃል፣ በኣልንም አምልከሃል የእስራኤልን መንግሥት ሕዝብ ሁሉ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ሰብስብ።”

OBS Image

450ዎቹ የበኣል ነቢያትን ጨምሮ የእስራኤል መንግሥት ሕዝብ ሁሉ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ መጡ። ኤልያስ ለሕዝቡ፣ “ስንት ጊዜ ዐሳባችሁን ትለውጣላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን አገልግሉ! በኣል አምላክ ቢሆን እርሱን አገልግሉ!” አላቸው።

OBS Image

ከዚያም ኤልያስ ለበኣል ነቢያት፣ “አንድ ወይፈን እረዱና መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡት፣ ነገር ግን እሳት አታንድዱ። እኔም እንደዚሁ አደርጋለሁ። በእሳት የሚመልስ አምላክ እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው” አላቸው። ስለዚህ የበኣል ካህናት መሥዋዕት አዘጋጁ ነገር ግን እሳት አላነደዱም።

OBS Image

ከዚያ በኋላ የበኣል ነቢያት “በኣል ሆይ፣ ስማን!” ብለው ወደ በኣል ጸለዩ። ቀኑን ሙሉ ጸለዩ፣ ጮኹ፣ እንዲሁም ሰውነታቸውን በቢላዋ ቈረጡ፣ ነገር ግን መልስ አልነበረም።

OBS Image

በመጨረሻ፣ ኤልያስ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አዘጋጀ። ከዚያም ሥጋው፣ እንጨቱ፣ እንዲሁም በመሠዊያው ዙሪያ ያለው መሬት እንኳ ፍጹም እስኪረጥብ ድረስ ዐሥራት ሁለት ጋን ሙሉ ውሃ በመሥዋዕቱ ላይ እንዲያፈሱ ለሕዝብ ነገራቸው።

OBS Image

ከዚያም ኤልያስ እንዲህ ብሎ ጸለየ፣ “ያህዌ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ፣ አንተ የእስራኤል አምላክ እንደ ሆንክና እኔም አገልጋይህ እንደ ሆንኩ ዛሬ ዐሳየን። አንተ እውነተኛ አምላክ እንደ ሆንክ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ መልስልኝ።”

OBS Image

ወዲያውኑ፣ እሳት ከሰማይ ወደቀና ሥጋውን፣ እንጨቱን፣ ድንጋዩን፣ ቈሻሻውን፣ እንዲሁም በመሠዊያው ዙሪያ የነበረውን ውሃ እንኳ አቃጠለ። ሕዝቡ ይህን ባዩ ጊዜ መሬት ላይ ወደቁና “ያህዌ አምላክ ነው! ያህዌ አምላክ ነው!” አሉ።

OBS Image

ከዚያም ኤልያስ፣ “ከበኣል ነቢያት አንድም እንዳያመልጥ!” አለ። ስለዚህ ሕዝቡ የበኣልን ነቢያት ያዙና ወስደው ገደሉአቸው።

OBS Image

ከዚያ በኋላ ኤልያስ ለንጉሥ አክዓብ፣ “ዝናብ መጥቶአልና ፈጥነህ ወደ ከተማ ተመለስ” አለው። ወዲያውኑ ሰማዩ ጠቈረ፣ ከባድ ዝናብም መዝነብ ጀመረ። ያህዌ ድርቁን አቆመው እውተኛ አምላክ መሆኑንም አረጋገጠ።

OBS Image

ከኤልያስ ዘመን በኋላ፣ እግዚአብሔር ነቢይ እንዲሆን ኤልሳዕ የተባለ ሰውን መረጠ። እግዚአብሔር በኤልሳዕ በኩል ብዙ ተአምራትን አደረገ። ከተአምራቱ አንዱ አስከፊ የቆዳ በሽታ በያዘው የጠላት ጦር ሠራዊት አዛዥ በነበረው ንዕማን ላይ ተከሠተ። ስለ ኤልሳዕ ሰምቶ ነበርና ስለዚህ እንዲፈውሰው ኤልሳዕን ሄዶ ጠየቀው። ኤልሳዕ በዮርዳኖስ ወንዝ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እንዲል ለንዕማን ነገረው።

OBS Image

በመጀመሪያ ንዕማን ተቈጣና ሞኝነት ስለ መሰለው ኤልሳዕ የነገረውን ነገር አላደረገውም። በኋላ ግን ዐሳቡን ለወጠና በዮርዳኖስ ወንዝ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ። በመጨረሻ ከውሃው በወጣ ጊዜ ቆዳው ፍጹም ተፈወሰ! እግዚአብሔር ፈወሰው።

OBS Image

እግዚአብሔር ሌሎች ብዙ ነቢያትን ላከ። ሁላቸውም ጣዖታትን ማምለክ እንዲያቆሙና ለሌሎች ፍትሕንና ምሕረትን ማሳየት እንዲጀምሩ ለሕዝቡ ነገሩአቸው። ነቢያቱ ክፉ መሥራትን ባያቆሙና ለእግዚአብሔር መታዘዝ ባይጀምሩ፣ እግዚአብሔር በበደለኝነት እንደሚፈርድባቸው፣ እንደሚቀጣቸውም ሕዝቡን አስጠነቀቁአቸው።

OBS Image

አብዛኛውን ጊዜ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር አልታዘዙም። ብዙውን ጊዜ ለነቢያት የነበራቸው አያያዝ መጥፎ ነበረ፣ አንዳንድ ጊዜም ይገደሉአቸው ነበር። በአንድ ወቅት፣ ነቢዩ ኤርምያስ ደረቅ በሆነ የውሃ ጕድጓድ ውስጥ ተጥሎ በዚያ እንዲሞት ተትቶ ነበር። በጕድጓዱ መጨረሻ በነበረው ጭቃ ውስጥ ገባ፣ ነገር ግን ያኔ ንጉሡ ራራለትና ከመሞቱ በፊት ከጕድጓዱ ጐትተው እንዲያወጡት አገልጋዮቹን አዘዛቸው።

OBS Image

ነቢያቱ ሕዝቡ ቢጡሉአቸውም እንኳ ስለ እግዚአብሔር መናራቸውን ቀጠሉ። ንስሐ ባይገቡ እግዚአብሔር እንደሚያጠፋቸው ሕዝቡን አስጠነቀቁአቸው። ደግሞም የእግዚአብሔር መሲሕ እንደሚመጣ ስለ ሰጠው ተስፋ ለሕዝቡ አስታወሱአቸው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከ1ኛ ነገሥት 16-18፤ 2ኛ ነገሥት 5፤ ኤርምያስ 38።