am_obs/content/17.md

8.1 KiB

17. እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን

OBS Image

ሳኦል የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ነበር። እርሱ ልክ ሕዝቡ እንደ ፈለጉት ረጅምና መልከ መልካም ነበር። ሳኦል እስራኤልን በገዛባቸው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ጥሩ ንጉሥ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ለእግዚአብሔር ያልታዘዘ ክፉ ሰው ሆነ፣ ስለዚህ እግዚአብሔር አንድ ቀን በሳኦል ቦታ ንጉሥ የሚሆን የተለየ ሰው መረጠ።

OBS Image

እግዚአብሔር ከሳኦል በኋላ ንጉሥ እንዲሆን ዳዊት የተባለ እስራኤላዊ ወጣት መረጠ። ዳዊት ከቤተ ልሔም ከተማ የሆነ የበጎች እረኛ ነበር። ዳዊት በተለያዩ ጊዜያት የአባቱን በጎች ሲጠብቅ፣ በጎቹን ያጠቁ አንበሳና ድብ ገድሎ ነበር። ዳዊት በእግዚአብሔር የሚያምንና ለእርሱም የሚታዘዝ ትሑትና ጻድቅ ሰው ነበር።

OBS Image

ዳዊት ታላቅ ወታደርና መሪ ሆነ። ዳዊት ገና ወጣት በነበረ ጊዜ ጎልያድ ተብሎ ከሚጠራ ግዙፍ ሰው ጋር ተዋጋ። ጎልያድ የሠለጠነ ወታደር፣ በጣም ብርቱ፣ እንዲሁም ቁመቱ ከሞላ ጎደል ሦስት ሜትር ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ጎልያድን ገድሎ እስራኤልን እንዲያድን ዳዊትን ረዳው። ከዚያ በኋላ ዳዊት በሕዝቡ የተመሰገነባቸውን፣ በእስራኤል ጠላቶች ላይ ብዙ ድሎችን አገኘ።

OBS Image

ሳኦል ሕዝቡ ለዳዊት በነበራቸው ፍቅር ቀና። ሳኦል ብዙ ጊዜ ዳዊትን ሊገድለው ሞከረ፣ ስለዚህ ዳዊት ከሳኦል ተሸሸገ። አንድ ቀን ሳኦል ይገድለው ዘንድ ዳዊትን እየፈለገው ነበር። ሳኦል ዳዊት ከእርሱ ይሸሸግበት ወደ ነበረው ዋሻ ሄደ፣ ነገር ግን ሳኦል አላየውም። ዳዊትም ወደ ሳኦል በጣም ተጠግቶ ነበርና ሊገድለው ይችል ነበር፣ ነገር ግን አልገደለውም። በዚህ ፈንታ ዳዊት ንጉሥ ለመሆን እንዳልገደለው ለሳኦል ለማረጋገጥ የሳኦልን ልብስ ዘርፍ ቈረጠ።

OBS Image

በመጨረሻ፣ ሳኦል በጦርነት ሞተ፣ ዳዊትም የእስራኤል ንጉሥ ሆነ። ዳዊት ጥሩ ንጉሥ ነበረ፣ ሕዝቡም ወደዱት። እግዚአብሔር ዳዊትን ባረከው፣ ስኬታማም አደረገው። ዳዊት ብዙ ጦርነቶችን ተዋጋ፣ የእስራኤልን ጠላቶች እንዲያሸንፍም እግዚአብሔር ረዳው። ዳዊት ኢየሩሳሌምን አሸንፎ ያዘና ዋና ከተማው አደረጋት። በዳዊት ንግሥና ጊዜ፣ እስራኤል ኃያልና ባለ ጠጋ ሆነች።

OBS Image

ዳዊት እስራኤላውያን ሁሉ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበትና ለእርሱ መሥዋዕቶችን የሚያቀርቡበት ቤተ መቅደስ ለመሥራት ፈለገ። ሕዝቡ ለ400 ዓመት ገደማ ሙሴ በሠራው የመገናኛ ድንኳን እግዚአብሔርን ያመልኩና መሥዋዕቶችን ያቀርቡለት ነበር።

OBS Image

ነገር ግን እግዚአብሔር ይህን መልእክት አስይዞ ነቢዩን ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፣ “አንተ የጦርነት ሰው ስለ ሆንክ ይህን ቤተ መቅደስ ለእኔ አትሠራልኝም። ልጅህ ይሠራዋል። ነገር ግን በእጅጉ እባርክሃለሁ። ከዝርያዎችህ አንዱ በሕዝቤ ላይ ንጉሥ ሆኖ ለዘላለም ይገዛል!” ለዘላለም የሚገዛው ብቸኛው የዳዊት ዝርያ፣ መሲሑ ነው። መሲሑ የዓምን ሕዝቦች ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው የእግዚአብሔር ምርጥ ነው።

OBS Image

ዳዊት እነዚህን ቃሎች በሰማ ጊዜ፣ ይህንን ታላቅ ክብርና ብዙ በረከቶችን ሊሰጠው ቃል ስለ ገባለት ወዲያውኑ እግዚአብሔርን አመሰገነ አወደሰም። ዳዊት እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች መቼ እንደሚያደርግ ዐላወቀም። ነገር ግን እንደ እውነቱ፣ እስራኤላውያን መሲሑ ከመምጣቱ በፊት ረዘም ላለ ጊዜ፣ ከሞላ ጐደል 1000 ዓመታት መጠበቅ ነበረባቸው።

OBS Image

ዳዊት በፍትሕና በታማኝነት ለብዙ ዓመታት ገዛ፣ እግዚአብሔርም ባረከው። ይሁን እንጂ፣ ወደ ሕይወቱ መጨረሻ በእግዚአብሔር ላይ ክፉኛ ኃጢአት ሠራ።

OBS Image

አንድ ቀን የዳዊት ወታደሮች በሙሉ ከቤታቸው ሄደው ጦርነት በሚዋጉበት ጊዜ፣ እርሱ ከቤተ መንግሥቱ ውጪ ሆኖ አንዲት ቆንጆ ሴት ገላዋን ስትታጠብ ዐየ። ስምዋ ቤርሳቤህ ነበር።

OBS Image

ዳዊት ፊቱን ወዲያ ከማዞር ፈንታ፣ ወደ እርሱ እንዲያመጣት ሰው ላከ። ከእርስዋ ጋር ተኛና ወደ ቤት መልሶ ላካት። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቤርሳቤህ አርግዣለሁ ብላ ወደ ዳዊት መልእክት ላከች።

OBS Image

ኦርዮ ተብሎ የሚጠራው የቤርሳቤህ ባል ከዳዊት ምርጥ ወታደሮች አንዱ ነበር። ዳዊት ኦርዮን ከጦርነቱ መልሶ ጠራውና ከሚስቱ ጋር እንዲሆን ነገረው። ነገር ግን ኦርዮ የቀሩት ወታደሮች በጦርነት ላይ እያሉ ወደ ቤት አልሄድም አለ። ስለዚህ ዳዊት ኦርዮን ወደ ጦርነቱ መልሶ ላከውና ይገደል ዘንድ ጠላት እጅግ በበረታበት ቦታ እንዲያሰልፈው ለጄነራሉ ነገረው።

OBS Image

ኦርዮ ከተገደለ በኋላ ዳዊት ቤርሳቤህን አገባት። በኋላ እርስዋ የዳዊትን ወንድ ልጅ ወለደች። እግዚአብሔር ዳዊት ስላደረገው ነገር በጣም ተቈጣ፣ ኃጢአቱ እንዴት ክፉ እንደ ነበረ ለዳዊት እንዲነግረው እግዚአብሔር ነቢዩን ናታንን ላከው። ዳዊት ኃጢአቱን ተናዘዘና እግዚአብሔር ይቅር አለው። ዳዊት በቀረው የሕይወቱ ዘመን በአስቸጋሪ ጊዜያት እንኳ፣ እግዚአብሔርን ተከተለ ታዘዘውም።

OBS Image

ነገር ግን ዳዊት ለሠራው ኃጢአት ቅጣት ሆኖ ልጁ ሞተ። ደግሞም በቀረው የሕይወቱ ዘመን በዳዊት ቤተ ሰብ ውጊያ ነበረ፣ የዳዊት ኃይልም በእጅጉ ተዳከመ። ዳዊት ለእግዚአብሔር ያልታመነ ቢሆንም እንኳ፣ እግዚአብሔር አሁንም ለተስፋዎቹ የታመነ ነበረ። በኋላ ዳዊትና ቤርሳቤህ ሌላ ወንድ ልጅ ወለዱ፣ ስሙንም ሰሎሞን አሉት።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከ1ኛ ሳሙኤል 10፡15-19፤ 24፤ 31፤ 2ኛ ሳሙኤል 5፤ 7፤ 11-12።