am_obs/content/15.md

6.6 KiB

15. የተስፋዪቱ ምድር

OBS Image

በመጨረሻ እስራኤላውያን ወደ ተስፋዪቱ ምድር፣ ወደ ከነዓን የሚገቡበት ጊዜ ደረሰ። ኢያሱ በብርቱ ግንብ ተጠብቃ ወደ ነበረችው የከነዓናውያን ከተማ ኢያሪኮ ሁለት ሰላዮችን ላከ። በዚያች ከተማ ሰላዮቹን የሸሸገችና ኋላ ላይ እንዲያመልጡ የረዳቻቸው ረዓብ የተባለች ጋለሞታ ትኖር ነበር። እርስዋ በእግዚአብሔር ስላመነች ይህን አደረገች። ሰላዮቹ፣ እስራኤላውያን ኢያሪኮን በሚያጠፉበት ጊዜ ረዓብንና ቤተ ሰብዋን እንደሚያድኑአቸው ቃል ገቡላት።

OBS Image

እስራኤላውያን ወደ ተስፋዪቱ ምድር ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ መሻገር ነበረባቸው። እግዚአብሔር፣ “መጀመሪያ ካህናቱ እንዲሻገሩ አድርግ” ብሎ ለኢያሱ ነገረው። ካህናቱ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መግባት በጀመሩ ጊዜ፣ እስራኤላውያን በደረቅ መሬት መሻገር ይችሉ ዘንድ ከላይ በኩል የነበረው ውሃ መፍሰሱን አቆመ።

OBS Image

ሕዝቡ የዮርዳኖስን ወንዝ ከተሻገሩ በኋላ፣ እግዚአብሔር ኃይለኛውን የኢያሪኮ ከተማ እንዴት እንደሚወጋት ለኢያሱ ነገረው። ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ታዘዙ። ወታደሮቹና ካህናቱ ልክ እግዚአብሔር እንደ ነገራቸው በቀን አንዴ ለስድስት ቀናት የኢያሪኮን ከተማ ዞሩ።

OBS Image

ከዚያም በሰባተኛው ቀን፣ እስራኤላውያን ሰባት ጊዜ ከተማይቱን ዞሩ። ለመጨረሻ ጊዜ ከተማዪቱን እየዞሩ እያሉ ወታደሮቹ ጮኹ፣ ካህናቱም መለከቶቻቸውን ነፉ።

OBS Image

ከዚያም በኢያሪኮ ዙሪያ የነበረው ግንብ ወደቀ! እግዚአብሔር እንዳዘዘው እስራኤላውያን በከተማይቱ የነበረውን ነገር ሁሉ አጠፉ። የእስራኤላውያን ወገን የሆኑትን ረዓብንና ቤተ ሰብዋን ብቻ አዳኑአቸው። በከነዓን የሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦች እስራኤላውያን ኢያሪኮን እንዳጠፉአት በሰሙ ጊዜ፣ እስራኤላውያን እነርሱንም ደግሞ እንደሚወጉአቸው በማሰብ ፈሩ።

OBS Image

እግዚአብሔር በከነዓን ካሉ ከማናቸውም የሕዝብ ወገኖች ጋር የሰላም ስምምነት እንዳያደርጉ እስራኤላውያንን አዞአቸው ነበር። ነገር ግን ገባዖናውያን የተባሉት ከከነዓናውያን ሕዝብ ወገኖች አንዱ የሆኑት፣ ከከነዓን ራቅ ብሎ ከሚገኝ ቦታ የመጡ መሆናቸውን ለኢያሱ ዋሽተው ነገሩት። ከእነርሱ ጋር የሰላም ስምምነት እንዲያደርግ ኢያሱን ጠየቁት። ገባዖናውያን ከየት እንደ ሆኑ ኢያሱና እስራኤላውያን እግዚአብሔርን አልጠየቁም። ስለዚህ ኢያሱ ከእነርሱ ጋር የሰላም ስምምነት አደረገ።

OBS Image

ገባዖናውያን እንዳታለሉአቸው ባወቁ ጊዜ፣ እስራኤላውያን ተናደዱ፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት የገቡት ቃል ስለ ነበር፣ ከእነርሱ ጋር ያደረጉትን የሰላም ስምምነት ጠበቁ። ቆየት ብሎ በሌላ ጊዜ፣ በከነዓን የነበሩ ሌላ ሕዝብ ወገን ነገሥታት፣ አሞራውያን፣ የገባዖን ሰዎች ከእስራኤላውያን ጋር የሰላም ስምምነት እንዳደረጉ ሰሙ፣ ስለዚህ ጦር ሠራዊታቸውን አንድ ላይ አስተባበሩና ገባዖናውያንን ወጉ። ገባዖናውያን እርዳታ ጥየቃ ወደ ኢያሱ መልእክት ላኩ።

OBS Image

ስለዚህ ኢያሱ የእስራኤልን ጦር ሠራዊት ሰበሰበና ወደ ገባዖናውያን ለመድረስ ሌሊቱን ሙሉ ተጓዙ። በማለዳ ሳያስቡት የአሞራውያንን ጦር ሠራዊት ወጉ።

OBS Image

በዚያን ቀን እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ተዋጋ። አሞራውያንን አደናገራቸውና ትልልቅ የበረዶ ድንጋይ ልኮ ከአሞራውያን ብዙዎችን ገደለ።

OBS Image

ደግሞ እግዚአብሔር እስራኤል አሞራውያንን ፈጽመው ለማሸነፍ በቂ ጊዜ ይኖራቸው ዘንድ ፀሐይ በሰማይ በአንድ ቦታ እንድትዘገይ አደረገ። በዚያን ቀን እግዚአብሔር ለእስራኤል ታላቅ ድል አጐናጸፋቸው።

OBS Image

እግዚአብሔር እነዚያን ጦር ሠራዊት ካሸነፈ በኋላ፣ ብዙዎቹ የከነዓናውያን ሕዝብ ወገኖች እስራኤልን ለመውጋት በአንድነት ተሰበሰቡ። ኢያሱና ሌሎቹ እስራኤላውያን ወጉና አሸነፉአቸው።

OBS Image

ከዚህ ጦርነት በኋላ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ነገድ ከተስፋዪቱ ምድር የሚደርሰውን ክፍል ሰጠው። ከዚያም እግዚአብሔር ለእስራኤል በድንበሮችዋ ሁሉ ሰላምን ሰጣት።

OBS Image

ኢያሱ ባረጀ ጊዜ፣ የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ አንድ ላይ ጠራ። ከዚያም ኢያሱ እግዚአብሔር በሲና ከእስራኤላውያን ጋር ላደረገው ቃል ኪዳን እንዲታዘዙ ለሕዝቡ ግዴታቸውን አስታወሳቸው። ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው ለመኖርና ሕግጋቱን ለመከተል ቃል ገቡ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከኢያሱ 1-24።