am_obs/content/14.md

63 lines
7.9 KiB
Markdown

# 14. በምድረ በዳ ተቅበዘበዙ
![OBS Image](https://cdn.door43.org/obs/jpg/360px/obs-en-14-01.jpg)
እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ክፍል ለሆኑት ሕግጋት እንዲታዘዙ ለእስራኤላውያን ከነገራቸው በኋላ፣ ከሲና ተራራ ሄዱ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከሲና ተራራ ከነዓን ተብላ ትጠራ ወደ ነበረችው ወደ ተስፋዪቱ ምድር ይመራቸው ጀመር። የደመናው ዓምድ ከፊት ለፊታቸው ወደ ከነዓን ሄደ፣ እነርሱም ተከተሉት።
![OBS Image](https://cdn.door43.org/obs/jpg/360px/obs-en-14-02.jpg)
እግዚአብሔር የተስፋዪቱን ምድር ለዘሮቻቸው እንደሚሰጣቸው ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ተስፋ ሰጥቶአቸው ነበር፣ ነገር ግን አሁን በዚያች ምድር ብዙ የሕዝብ ወገኖች ይኖሩ ነበር። እነርሱም ከነዓናውያን ተብለው ይጠሩ ነበር። ከነዓናውያን እግዚአብሔርን አላመለኩትም ወይም አልታዘዙትም። ሐሰተኞች አማልክትን አመለኩ ብዙ ነገሮችንም አደረጉ።
![OBS Image](https://cdn.door43.org/obs/jpg/360px/obs-en-14-03.jpg)
እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሎ ነገራቸው፣ “በተስፋዪቱ ምድር ያሉትን ከነዓናውያንን ሁሉ አጥፉአቸው። ከእነርሱ ጋር ሰላምን አታድርጉ አታግቡአቸውም። ጣዖቶቻቸውን ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉአቸው። ለእኔ ባትታዘዙ፣ በእኔ ፈንታ የእነርሱን ጣዖታት ታመልካላችሁ።”
![OBS Image](https://cdn.door43.org/obs/jpg/360px/obs-en-14-04.jpg)
እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ድንበር በደረሱ ጊዜ፣ ሙሴ ከእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ አንድ አንድ ሰው፣ ዐሥራ ሁለት ሰዎችን መረጠ። ሄደው ምድሪቱ ምን እንደምትመስል እንዲሰልሉ መመሪያ ሰጣቸው። እነዚህ ሰዎች፣ ብርቱዎች ወይም ደካሞች መሆናቸውን ለማየት ከነዓናውያንን ደግሞ መሰለል ነበረባቸው።
![OBS Image](https://cdn.door43.org/obs/jpg/360px/obs-en-14-05.jpg)
ዐሥራ ሁለቱ ሰዎች በከነዓን ለአርባ ቀን ተጓዙና ተመልሰው መጡ። “ምድሪቱ በጣም ለም ነች ሰብሉም የተትረፈረፈ ነው!” ብለው ለሕዝቡ ነገሩአቸው። ዐሥሩ ሰላዮች ግን፣ “ከተሞቹ በጣም ብርቱዎች ሰዎቹም የገዘፉ ናቸው! ብንወጋቸው በእርግጥ ያሸንፉናል ይገድሉናልም!” አሉ።
![OBS Image](https://cdn.door43.org/obs/jpg/360px/obs-en-14-06.jpg)
ወዲያውኑ ሌሎቹ ሁለት ሰላዮች፣ ካሌብና ኢያሱ፣ “የከነዓን ሰዎች ረጃጅሞችና ብርቱዎች መሆናቸው እውነት ነው፣ ነገር ግን እኛ በእርግጥ እናሸንፋቸዋለን! እግዚአብሔር ስለ እኛ ይዋጋል!” አሉ።
![OBS Image](https://cdn.door43.org/obs/jpg/360px/obs-en-14-07.jpg)
ሕዝቡ ግን ካሌብንና ኢያሱን አልሰሙአቸውም። ሙሴንና አሮንን ተቈጡአቸውና፣ “ወደዚህ አስከፊ ቦታ ለምን አመጣችሁን? በጦርነት ከምንሞትና ሚስቶቻችን እንዲሁም ልጆቻችን ባሮች ከሚሆኑ ይልቅ በግብፅ ብንኖር ይሻለን ነበር” አሉ። ሕዝቡ ወደ ግብፅ መልሶ የሚወስዳቸው የተለየ መሪ ለመምረጥ ፈለጉ።
![OBS Image](https://cdn.door43.org/obs/jpg/360px/obs-en-14-08.jpg)
እግዚአብሔር በጣም ተቈጣና ወደ መገናኛው ድንኳ መጣ። እንዲህም አለ፣ “እናንተ በእኔ ላይ ስላመፃችሁ፣ ሕዝቡ ሁሉ በምድረ በዳ ይቅበዘበዛሉ። ከኢያሱና ከካሌብ በቀር ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሁሉ በዚያ ይሞታሉ እንጂ ከቶ ወደ ተስፋዪቱ ምድር አይገቡም።”
![OBS Image](https://cdn.door43.org/obs/jpg/360px/obs-en-14-09.jpg)
ሕዝቡ ይህን በሰሙ ጊዜ፣ ኃጢአት በመሥራታቸው ዐዘኑ። የጦር መሣሪያዎቻቸውን ይዘው የከነዓንን ሰዎች ለመውጋት ሄዱ። ሙሴ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ስላልነበረ እንዳይሄዱ አስጠነቀቃቸው፣ ነገር ግን እርሱን አልሰሙትም።
![OBS Image](https://cdn.door43.org/obs/jpg/360px/obs-en-14-10.jpg)
እግዚአብሔር አብሮአቸው ወደ ጦርነቱ አልሄደም፣ ስለዚህ ተሸነፉ ብዙዎቻቸውም ተገደሉ። ከዚያም እስራኤላውያን ከከነዓን ተመለሱና በምድረ በዳ ለአርባ ዓመት ተቅበዘበዙ።
![OBS Image](https://cdn.door43.org/obs/jpg/360px/obs-en-14-11.jpg)
የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ በተቅበዘበዙባቸው አርባ ዓመታት እግዚአብሔር መገባቸው። ከሰማይ “መና” ተብሎ የሚጠራ እንጀራ ሰጣቸው። ደግሞም ሥጋ ይበሉ ዘንድ ወደ ሰፈራቸው ድርጭቶች ላከላቸው። በዚያን ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር ልብሳቸውና ጫማቸው እንዳያልቅ አደረገ።
![OBS Image](https://cdn.door43.org/obs/jpg/360px/obs-en-14-12.jpg)
እግዚአብሔር ተአምራዊ በሆነ መንገድ ውሃ እንኳ ከአለት ሰጣቸው። ይህም ሁሉ ሆኖ ግን የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ አማረሩ አጕረመረሙም። ቢሆንም፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ለሰጠው ተስፋ አሁንም የታመነ ነበር።
![OBS Image](https://cdn.door43.org/obs/jpg/360px/obs-en-14-13.jpg)
ሕዝቡ ምንም ውሃ ባልነበራቸው በሌላ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ለሙሴ፣ “አለቱን ተናገረው፣ ከእርሱም ውሃ ይወጣል” አለው። ነገር ግን ሙሴ ለአለቱ በመናገር ፈንታ በበትር ሁለት ጊዜ ስለመታው በሕዝቡ ሁሉ ፊት እግዚአብሔርን አዋረደ። ሁለም ሰው እንዲጠጣ ከአለቱ ውሃ ወጣ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር በሙሴ ላይ ተቈጣና፣ “ወደ ተስፋዪቱ ምድር አትገባም” አለው።
![OBS Image](https://cdn.door43.org/obs/jpg/360px/obs-en-14-14.jpg)
እስራኤላውያን ለአርባ ዓመት በምድረ በዳ ከተቅበዘበዙ በኋላ፣ በእግዚአብሔር ላይ ያመፁት ሁሉ ሞቱ። ከዚያም እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደ ገና ወደ ተስፋዪቱ ምድር ዳርቻ መራቸው። አሁን ሙሴ አርጅቶ ነበር፣ ስለዚህ ሕዝቡን በመምራት እንዲያግዘው እግዚአብሔር ኢየሱን መረጠ። ደግሞም እግዚአብሔር አንድ ቀን እንደ ሙሴ ያለ ሌላ ነቢይ እንደሚልክ ለሙሴ ተስፋ ሰጠው።
![OBS Image](https://cdn.door43.org/obs/jpg/360px/obs-en-14-15.jpg)
ከዚያም እግዚአብሔር የተስፋዪቱን ምድር ለማየት ይችል ዘንድ ወደ ተራራ ራስ ላይ እንዲወጣ ለሙሴ ነገረው። ሙሴ የተስፋዪቱን ምድር ዐየ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ወደ እርስዋ እንዲገባ አልፈቀደለትም። ከዚያም ሙሴ ሞተ፣ እስራኤላውያንም ለሠላሳ ቀናት ዐዘኑ። ኢያሱ ዐዲሱ መሪአቸው ሆነ። ኢያሱ በእግዚአብሔር ያመነና የታዘዘውም ስለ ነበር ጥሩ መሪ ነበር።
_የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘጸአት 16-17፤ ዘኍልቁ 10-14፤ 20፤ 27፤ ዘዳግም 34።_