am_obs/content/13.md

6.7 KiB

13. እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን

OBS Image

እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በቀይ ባሕር በኩል ከመራቸው በኋላ፣ በምድረ በዳ በኩል ሲና ተብሎ ወደሚጠራ ተራራ ወሰዳቸው። ይህም ሙሴ የሚቃጠለውን ቊጥቋጦ ያየበት ተራራ ነው። ሕዝቡ በተራራው ሥር ድንኳኖቻቸውን ተከሉ።

OBS Image

እግዚአብሔር፣ “ለእኔ ብትታዘዙና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ፣ የከበረ ርስት፣ የንጉሥ ካህናት፣ እንዲሁም ቅዱስ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ” ብሎ ለሙሴና ለእስራኤል ሕዝብ ተናገረ።

OBS Image

ሕዝቡ በመንፈሳዊ በኩል ራሳቸውን ካዘጋጁ ከሦስት ቀን በኋላ፣ እግዚአብሔር በነጐድጓድ፣ በመብረቅ፣ በጢስ እንዲሁም ከፍ ባለ የመለከት ድምፅ በሲና ተራራ ላይ ወረደ። ወደ ተራራው እንዲወጣ የተፈቀደው ለሙሴ ብቻ ነበር።

OBS Image

ከዚያም እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ሰጣቸውና እንዲህ አለ፣ “እኔ ከግብፅ ባርነት ያዳንኳችሁ፣ አምላካችሁ፣ ያህዌ ነኝ። ሌሎችን አማልክት አታምልኩ።”

OBS Image

“ጣዖታትን አትሥራ አታምልካቸውም፣ ምክንያቱም እኔ፣ ያህዌ ቀናተኛ አምላከ ነኝ። ስሜን በከንቱ አትጥራ፣ የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ ዐስብ። ይኸውም ሥራህን ሁሉ በስድስት ቀን ሥራ፣ ምክንያቱም ሰባተኛው ቀን የምታርፍበትና እኔን የምታስታውስበት ዕለት ነው።”

OBS Image

“አባትህንና እናትህን አክብር። አትግደል። አታመንዝር። አትስረቅ። አትዋሽ። የባልንጀራህን ሚስት፣ ቤቱን፣ ወይም የእርሱ የሆነውን ማንኛውም ነገር ለመውሰድ አትመኝ።”

OBS Image

ከዚያም እግዚአብሔር እነዚህን ዐሥር ትእዛዛት በሁለት ጠፍጣፋ ድንጋዮች ላይ ጽፎ ለሙሴ ሰጠው። ደግሞ እግዚአብሔር የሚከተሉአቸው ሌሎች ብዙ ሕግጋትንና ደንቦችን ሰጣቸው። ሕዝቡ እነዚህን ሕግጋት ከፈጸሙ እግዚአብሔር እንደሚባርካቸውና እንደሚጠብቃቸው ተስፋ ሰጠ። ሕግጋቱን ካልፈጸሙ ግን እግዚአብሔር ይቀጣቸዋል።

OBS Image

ደግሞም እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን እንዲሠሩት ስለሚፈልገው ድንኳን መግለጫ ሰጣቸው። እርሱ የመገናኛው ድንኳ ተብሎ ይጠራ ነበር፣ በትልቅ መጋረጃ የተከፈሉ ሁለት ክፍሎችም ነበሩት። እግዚአብሔር በዚያ ይኖር ስለ ነበረ፣ ከመጋረጃ በስተጀርባ ወዳለው ክፍል እንዲገባ የተፈቀደለት ሊቀ ካህን ብቻ ነበር።

OBS Image

የእግዚአብሔርን ሕግ ያልፈጸመ ማንኛውም ሰው በመገናኛው ድንኳ ፊት ለፊት ወዳለው መሠዊያ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት የሚሆን እንስሳ ማምጣት ይችል ነበር። ካህኑ እንስሳውን ያርድና በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው ነበር። የተሠዋው እንስሳ ደም የሰውዬውን ኃጢአት ይሸፍንና ያንን ሰው በእግዚአብሔር ፊት ያነጻው ነበር። እግዚአብሔር ካህናቱ ይሆኑ ዘንድ የሙሴን ወንድም አሮንን፣ እንዲሁም የአሮንን ዝርያዎች መረጠ።

OBS Image

ሕዝቡ ሁላቸውም እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትእዛዛት ለመፈጸም፣ እግዚአብሔርን ብቻ ለማምለክ፣ እንዲሁም የተለዩ ሕዝቡ ለመሆን ተስማሙ። ነገር ግን ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ ቃል ከገቡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ክፉኛ ኃጢአት ሠሩ።

OBS Image

ሙሴ ለብዙ ቀናት በሲና ተራራ ጫፍ ላይ ሆኖ ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገር ነበር። ሕዝቡ እርሱ እስኪመለስ ድረስ መጠባበቅ ሰለቻቸው። ስለዚህ ወደ አሮን ወርቅ አመጡና ጣዖት እንዲሠራላቸው ጠየቁት!

OBS Image

አሮን በጥጃ ቅርፅ የወርቅ ጣዖት ሠራ። ሕዝቡ ከቊጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ ጣዖቱን ማምለክ ጀመሩ፣ መሥዋዕትም ሠዉለት! በኃጢአታቸው ምክንያት እግዚአብሔር በጣም ተቈጣቸው፣ ሊያጠፋቸውም ዐቀደ። ነገር ግን ሙሴ ጸለየላቸው፣ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰማ እነርሱን አላጠፋቸውም።

OBS Image

ሙሴ ከተራራው በወረደና ጣዖቱን ባየ ጊዜ፣ በጣም ተቈጥቶ እግዚአብሔር ዐሥሩን ትእዛዛት የጻፈባቸውን ድንጋዮች ሰባበረ።

OBS Image

ከዚያም ሙሴ ጣዖቱን ፈጨው፣ በውሃውም ላይ በተነው፣ ለሕዝቡም አጠጣቸው። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ መቅሠፍት ላከና ብዙዎቻቸው ሞቱ።

OBS Image

ሙሴ እንደ ገና ተራራው ላይ ወጣና እግዚአብሔር ሕዝቡን ይቅር እንዲላቸው ጸለየ። እግዚአብሔር ሙሴን ሰማውና ይቅር አላቸው። ሙሴ የሰባበራቸውን ለመተካት በዐዲስ ጠፍጣፋ ድንጋዮች ላይ ዐሥሩን ትእዛዛት ጻፈ። ከዚያም እግዚአብሔር እስራኤላውያን ከሲና ተራራ ወደ ተስፋዪቱ ምድር መራቸው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘጸአት 19-34።