am_obs/content/12.md

6.3 KiB

12. የእስራኤላውያን ከግብፅ መውጣት

OBS Image

እስራኤላውያን ከግብፅ በመውጣታቸው በጣም ደስ አላቸው። ከእንግዲህ ባሪያዎች አይደሉም፣ ወደ ተስፋዪቱ ምድርም በመጓዝ ላይ ነበሩ! ግብፃውያን ለእስራኤላውያን ወርቅና ብር ሌሎችም የከበሩ ነገሮች ሳይቀሩ የጠየቁትን ማንኛውንም ነገር ሰጡአቸውና ከግብፅ ሲወጡ ከሌሎች ብሔሮች የሆኑ አንዳንድ ሰዎች በእግዚአብሔር አምነው ከእስራኤላውያን ጋር ሄዱ።

OBS Image

እግዚአብሔር በፊታቸው በሚሄድ ቀን ረጅም በሆነ የደመና ዓምድ፣ ማታም ረጅም በሆነ የእሳት ዓምድ መራቸው። እግዚአብሔር ሁልጊዜ ከእነርሱ ጋር ነበርና ሲጓዙ መራቸው። ማድረግ ያለባቸው ነገር ቢኖር እርሱን መከተል ብቻ ነበር።

OBS Image

ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ፈርዖንና ሕዝቡ ዐሳባቸውን ለወጡና እስራኤላውያን እንደ ገና የእነርሱ ባሪያዎች እንዲሆኑ ፈለጉ። እግዚአብሔር ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን ሕዝቡ እንዲያዩ፣ እንዲሁም እርሱ፣ ያሕዌ፣ ከፈርዖንና ከአማልክቱ የበለጠ ኃያል እንደ ሆነ ይረዱ ዘንድ ፈርዖንን ዐሳበ ግትር አደረገው።

OBS Image

ስለዚህ ፈርዖንና ጦር ሠራዊቱ እንደ ገና ባሪያዎቻቸው ሊያደርጉአቸው እስራኤላውያንን አሳደዱአቸው። እስራኤላውያን የግብፅ ጦር ሠራዊት ሲመጣ ባዩ ጊዜ፣ በፈርዖን ጦር ሠራዊትና በቀይ ባሕር መካከል እንደ ተጠመዱ ዐወቁ። በጣም ፈርተው ስለ ነበር፣ “ከግብፅ ለምን ወጣን? መሞታችን ነው!” ብለው ጮኹ።

OBS Image

ሙሴ እስራኤላውያንን፣ “አትፍሩ! ዛሬ እግዚአብሔር ይዋጋላችሁና ያድናችኋል” ብሎ ነገራቸው። ከዚያም እግዚአብሔር፣ “ወደ ቀይ ባሕር እንዲንቀሳቀሱ ለሕዝቡ ንገራቸው” ብሎ ለሙሴ ነገረው። ከዚያም እግዚአብሔር ግብፃውያን እስራኤላውያንን ማየት እንዳይችሉ የደመናውን ዓምድ በእስራኤላውያንና በግብፃውያን መካከል አደረገው።

OBS Image

እግዚአብሔር ለሙሴ በባሕሩ ላይ እጁን እንዲዘረጋና ውሃውን እንዲከፍለው ነገረው። ከዚያም እግዚአብሔር በባሕሩ መተላለፊያ መንገድ ይኖር ዘንድ ውሃውን ነፋስ ወደ ግራና ወደ ቀኝ እንዲያንቀሳቅሰው አደረገ።

OBS Image

እግዚአብሔር ለሙሴ በባሕሩ ላይ እጁን እንዲዘረጋና ውሃውን እንዲከፍለው ነገረው። ከዚያም እግዚአብሔር በባሕሩ መተላለፊያ መንገድ ይኖር ዘንድ ውሃውን ነፋስ ወደ ግራና ወደ ቀኝ እንዲያንቀሳቅሰው አደረገ።

OBS Image

እስራኤላውያን ውሃው በግራና በቀኛቸው ግድግዳ ሆኖላቸው በባሕሩ በደረቅ መሬት ላይ ተጓዙ።

OBS Image

ከዚያም እግዚአብሔር ግብፃውያኑ እስራኤላውያን ማምለጣቸውን ያዩ ዘንድ ደመናውን ከመንገዱ ወደ ላይ አንቀሳቀሰው። ግብፃውያን ከኋላቸው ሆነው ሊያሳድዱአቸው ወሰኑ።

OBS Image

ስለዚህ በባሕሩ መንገድ እስራኤላውያንን ተከተሉአቸው፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ግብፃውያን እንዲጨነቁና ሰረገሎቻቸውም እንዲታሰሩ አደረገ። “ሽሹ! እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን እየተዋጋላቸው ነው!” ብለው ጮኹ።

OBS Image

እስራኤላውያን ባሕሩን በደኅና ከተሻገሩ በኋላ፣ እግዚአብሔር እንደ ገና እጁን እንዲዘረጋ ለሙሴ ነገረው። እርሱም በታዘዘ ጊዜ፣ ውሃው በግብፃውያን ሠራዊት ላይ ተመለሰና እንደ መጀመሪያው ሆነ። መላው የግብፃውያን ጦር ሠራዊት ሰጠመ።

OBS Image

እስራኤላውያን ግብፃውያን እንደ ሞቱ ባዩ ጊዜ በእግዚአብሔር አመኑ ሙሴም የእግዚአብሔር ነቢይ መሆኑን አመኑ።

OBS Image

ደግሞም እስራኤላውያን እግዚአብሔር ከሞትና ከባርነት ስለ አዳናቸው በብዙ ደስታ ደስ አላቸው! አሁን እግዚአብሔርን ለማገልገል ነጻ ሆኑ። እስራኤላውያን እርሱ ከግብፃውያን ጦር ሠራዊት ስለ አዳናቸው ዐዲሱን ነጻነታቸውን ለማክበርና እግዚአብሔርን ለማመስገን ብዙ መዝሙሮችን ዘመሩ።

OBS Image

እንዴት እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ድልን እንደ ሰጣቸውና ባሪያዎች ከመሆን እንዳዳናቸው ያስታውሱ ዘንድ በያመቱ ፋሲካን እንዲያከብሩ እስራኤላውያንን አዘዛቸው። ፍጹም የሆነ ጠቦት አርደው ካልቦካ ቂጣ ጋር በመብላት ተደሰቱ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘጸአት 12፡33-15፡21።