am_obs/content/08.md

6.0 KiB

8. እግዚአብሔር ዮሴፍንና ቤተ ሰቡን አዳነ

OBS Image

ከብዙ ዓመታት በኋላ ያዕቆብ ባረጀ ጊዜ የከብቶቹን መንጋ የሚጠብቁት ወንድሞቹ እንዴት እንዳሉ እንዲያያቸው የሚወደው ልጁን ዮሴፍን ላከው።

OBS Image

አባታቸው ያዕቆብ ዮሴፍን ከወንድሞቹ ሁሉ አብዝቶ ይወድደው ስለ ነበረና አለቃቸው እንደሚሆን ሕልም አልሞ ስለ ነበር የዮሴፍ ወንድሞች ጠሉት። ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በመጣ ጊዜ ጠልፈውት ለባሪያ ነጋዴዎች ሸጡት።

OBS Image

የዮሴፍ ወንድሞች ወደ ቤት ከመመለሳቸው በፊት የዮሴፍን ቀሚስ ቀድደው በፍየል ደም ነከሩት። ከዚያም በደም የተነከረውን የዮሴፍን ቀሚስ ለአባታቸው አሳዩት። እርሱም የዱር አውሬ ዮሴፍን ገድሎታል ሲል አሰበ፤ ያዕቆብም በጣም አዘነ።

OBS Image

የባሪያ ነጋዴዎቹ ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት። በዚያን ጊዜ ግብፅ በአባይ ወንዝ አጠገብ የምትገኝ ታላቅና ኃያል አገር ነበረች። የባሪያ ነጋዴዎቹ ዮሴፍን ባርያ አድርገው ለሀብታም የመንግሥት ባለ ሥልጣን ሸጡት። ዮሴፍ ጌታውን በደንብ አድርጎ አገለገለው። እግዚአብሔርም ዮሴፍን ባረከው።

OBS Image

የጌታው ሚስት ከዮሴፍ ጋር ለመተኛት ሞከረች። ዮሴፍ ግን በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት አልሠራም ሲል እምቢ አላት። እሷም ስለ ተናደደችበት በሐሰት ከስሳው ተይዞ ወደ እሥር ቤት ተወሰደ በእሥር ቤትም ቢሆን ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ ስለ ተገኘ እግዚአብሔር ባረከው።

OBS Image

ምንም እንኳ ዮሴፍ ንጹሕ ሰው ቢሆንም ከሁለት ዓመት በኋላ አሁንም በእሥር ቤት ነበር። አንድ ሌሊት ግብፃውያን ‘ንጉሣችን’ የሚሉት ፈርዖን በጣም የታወከባቸውን ሁለት ሕልሞች አለመ። ከአማካሪዎቹ አንዳቸውም የሕልሙን ትርጕም ሊነግሩት አልቻሉም።

OBS Image

እግዚአብሔር ለዮሴፍ ሕልም የመተርጐም ችሎታ ሰጥቶት ነበር፤ ስለዚህ ፈርዖን ዮሴፍን ከእሥር ቤት ወደ ራሱ አስመጣው። ዮሴፍ ሕልሙን ተረጐመለትና እንዲህ አለው። “እግዚአብሔር ሰባት የጥጋብ ዓመታትን ይልካል፣ ቀጥሎም ሰባት የረሀብ ዓመታት ይሆናሉ” አለ።

OBS Image

ፈርዖንም በዮሴፍ በጣም ተገረመ፣ በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ከእርሱ ቀጥሎ ሁለተኛ ባለ ሥልጣን አድርጎ ሾመው።

OBS Image

ዮሴፍም ሕዝቡን በሰባቱ የመልካም ምርት ዓመታት በርካታ እህል በጎተራው እንዲያከማቹ ነገራቸው። የሰባቱ የረሀብ ዓመታት በመጡ ጊዜ ዮሴፍ ከጎተራው ለሕዝቡ እህል በመሸጡ በቂ የሚበላ ምግብ አገኙ።

OBS Image

የረሀቡ አስከፊነት በግብፅ ብቻ ሳይሆን፣ ያዕቆብና ቤተ ሰቡ በሚኖሩበት በከነዓን ምድር ደግሞ ነበር።

OBS Image

ያዕቆብ ልጆቹ እህል እንዲሸምቱ ወደ ግብፅ ላካቸው። የዮሴፍ ወንድሞች ለእህል ሸመታ ሄደው ፊቱ በቆሙ ጊዜ ዮሴፍ መሆኑን አላስተዋሉትም ዮሴፍ ግን አውቋቸዋል።

OBS Image

ዮሴፍ ወንድሞቹን ከፈተናቸው በኋላ ተለውጠው እንደ ሆነ ለማየት እንዲህ አላቸው፣ “አትፍሩ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ ለባርነት ስትሸጡኝ ክፉ ልታደርጉብኝ ሞከራችሁ ነገር ግን እግዚአብሔር ክፉውን ለመልካም አደረገው መጥታችሁ በግብፅ ኑሩ እኔም ለእናንተና ለቤተ ሰቦቻችሁ የሚያስፈልጋችሁን አቀርብላችኋለሁ።”

OBS Image

የዮሴፍ ወንድሞች ወደአገራቸው ተመልሰው ዮሴፍ በሕይወት መኖሩን ለአባታቸውለያዕቆብ በነገሩት ጊዜ ያዕቆብበጣም ደስ አለው።

OBS Image

ምንም እንኳ ያዕቆብ ሽማግሌ ቢሆንም ከመላው ቤተሰቡ ጋር ወደ ግብፅ ሄዶ በዚያ ኖሩ። ያዕቆብ ከመሞቱ በፊት ልጆቹን እያንዳንዳቸውን ባረካቸው።

OBS Image

እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባቸው የቃል ኪዳን ተስፋዎች ወደ ይስሐቅ ተላለፉ፤ ከዚያም ወደ ያዕቆብ፣ ቀጥሎም ወደ ዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆቹና ቤተ ሰቦቻቸው ተላለፈ። የዐሥራ ሁለቱ ልጆች ዘሮቻቸው ዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ሆኑ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘፍጥረት 37-50።