am_obs/content/02.md

5.6 KiB

2. ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ

OBS Image

አዳምና ሚስቱ እግዚአብሔር በሠራላቸው የአትክልት ስፍራ ሲኖሩ በጣም ደስተኞች ነበሩ። ሁለቱም ራቁታቸውን ነበሩ ይሁን እንጂ ራቁታቸውን መሆናቸው እንዲተፋፈሩ አላደረጋቸውም፤ ምክንያቱም ኃጢአት በዓለም አልነበረም። እነርሱም በአትክልቱ ስፍራ እየተመላለሱ ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገሩ ነበር።

OBS Image

ነገር ግን ተንኮለኛ እባብ በአትክልቱ ውስጥ ነበር። ሴትየዋንም ጠየቃት “እግዚአብሔር በእርግጥ በአትክልቱ ውስጥ ካለው ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ ብሎችኋልን?” አላት።

OBS Image

ሴቲቱም፣ “እግዚአብሔር ክፉንና መልካሙን ከሚያሳውቀው የእውቀት ዛፍ በስተቀር ከማንኛውም የዛፍ ፍሬ መብላት እንደምንችል ተናግሮናል። ነገር ግን ያንን ፍሬ ብትበሉ ወይም ብትነኩት እንኳ ትሞታላችሁ” አለን።

OBS Image

እባቡም ለሴቲቱ መልሶ፣ “ይህ እውነት አይደለም አትሞቱም ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዓይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ እንደ እግዚአብሔርእንደምትሆኑ እግዚአብሔርስለሚያውቅ ነው አትብሉት ያላችሁ” አለ።

OBS Image

ሴቲቱ የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዓይን የሚያስደስትና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደ ሆነ ባየች ጊዜ ከፍሬው ወስዳ በላች። ከእርሷም ጋር ለነበረው ለባሏም ሰጠችው። እርሱም ከዛፉ ፍሬ በላ።

OBS Image

ወዲያውም የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ። ራቁታቸውን መሆናቸውንም ተገነዘቡ፤ ቅጠልም እንደ ልብስ ሰፍተው ገላቸውን ለመሸፈን ሞከሩ።

OBS Image

ሰውዬውና ሚስቱም የእግዚአብሔር ድምፅ በአትክልቱ መካከል ሲመላለስ ሰምተው ሁሉም ከእግዚአብሔር ፊት ተሸሸጉ። እግዚአብሔርም አዳምን ጠርቶ “የት ነህ?” አለው። አዳምም “በአትክልቱ ስፍራ ስትመላለስ ሰማሁ ራቁቴን ስለ ሆንኩ ፈራሁ ተሸሸግሁም” ብሎ መለሰ።

OBS Image

እግዚአብሔርም “ራቁትህን መሆንህን ማን ነገረህ? ከርሱ እንዳትበላ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህን?” አለው። አዳምም፣ “ይህች ከእኔ ጋር እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለው። እግዚአብሔር ሴቲቱንም ይህ ያደረግሽው ምንድን ነው?" አላት። እርሷም፣ “እባብ አሳሳተኝና በላሁ” አለች።

OBS Image

እግዚአብሔር እባቡን እንዲህ አለው፤ “የተረገምህ ነህ፣ በደረትህ ትሳባለህ አፈርም ትበላለህ አንተና ሴቲቱ ጥለኞች ትሆናላችሁ የአንተ ልጆችና የእርሷም ልጆች እንዲሁ ጥለኞች ይሆናሉ የሴቲቱ ዘር ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ተረከዙን ታቆስላለህ።”

OBS Image

እግዚአብሔር ሴቲቱንም አላት “በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፣ ፍላጎትሽ ወደ ባልሽ ይሆናል እርሱም የበላይሽ ይሆናል።”

OBS Image

እግዚአብሔርም አዳምን እንዲህ አለው። “የሚስትህን ቃል ሰምተህ አትብላ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ ፍሬ በልተሃልና ምድር ካንተ የተነሣ ተረግማለች። በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ምግብህን ጥረህ ግረህ ከእርሷ ታገኛለህ። ከዚያም ትሞታለህ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ።” አዳምም ሚስቱን የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና ሔዋን ብሎ ጠራት ትርጓሜውም ሕይወት ሰጪ ማለት ነው፤ እግዚአብሔርም ከእንስሳ ቆዳ አዘጋጅቶ አዳምንና ሔዋንን አለበሳቸው።

OBS Image

እግዚአብሔርም ሰው መልካምንና ክፉን ለይቶ በማወቅ ረገድ አሁን ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል አሁን ደግሞ እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ፍሬ ቀጥፎ እንዳይበላና ለዘላለምም እንዳይኖር አዳምና ሔዋንን ከውቡ የአትክልት ስፍራ አስወጣቸው። ከዚያም ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅና ማንም ከዚህ የሕይወት ዛፍ ቀጥፎ እንዳይበላ ኃይለኞች መላእክትን በአትክልቱ ስፍራ አኖረ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ዘፍጥረት 3